ከወተት ተዋጽኦ የሚገኘውን ምርት ለማሳደግ የእንሳሰት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት እየተቋቋመ ነው

1063
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 በኢትዮጵያ ከወተትና ከወተት ተዋጽኦ የሚገኘውን ምርት ለማሳደግ የእንሳሰት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት እየተቋቋመ መሆኑን የግብርናና እንስሳት ኃብት ሚኒስቴር ገለጸ። የዓለም አቀፉ የወተት ቀን ''የወተት ኩባያችንን እናንሳ'' በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ ወተት 14 በመቶ የሚሆነውን የግብርና ንግድ ድርሻ ቢይዝም በእንስሳት ኃብት ቁጥርና ምርታማነት አለመጣጣም የተነሳ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች ድርሻ ዝቅተኛ ነው። በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ልቀው የሄዱ ሌሎች አገሮች በቀን ከአንዲት ላም ብቻ እስከ 50 ሊትር ወተት ሲሰበስቡ በኢትዮጵያ አንዲት ላም በቀን የምትሰጠው የወተት መጠን በአማካይ 1 ነጥብ 5 ሊትር ብቻ ነው። በስነ-ስርዓቱ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ ዶክተር ስንታየሁ ይግረም እንደሚሉት፤ ምርታማነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ቴክኖሎጂ ያስደገፉ እስራኤልን የመሰሉ አገሮች ከአንድ ላም በዓመት እስከ 11 ሺህ ሊትር ወተት ያገኛሉ። “በኢትዮጵያ ያለው የቀንድ ከብቶች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም ምርታማነቱ ዝቅተኛ ነው፤ ለዚህም ዋናው ምክንያት በአገሪቱ የከብት እርባታ የሚካሄደው ራሱን ችሎ ሳይሆን በጥምር ግብርና ውስጥ ተወስኖ በመሆኑ ነው፤" በማለት ገልፀዋል። የወተት ኃብት ልማትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች በአግባቡ ከተከናወኑ የውጭ ምንዛሬ ከማዳን ባለፈ ዘርፉ ለአገራዊ ምርት እድገት ጉልህ ሚና እንዲጫወት ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል። “ይህን ለማድረግ ግን ወተትን በጥራትና በብዛት እንደዚሁም በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ይገባል'' ያሉት ዶክተር ስንታየሁ በመስኩ ኢንቨስትመንትን በማመረታታት የሥራ ዕድልን መፍጠርም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል። በቀጣይም ከዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማግኘት ዩኒቨርሲቲዎችና የጥናትና ምርምር ተቋማት ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸው የጠቆሙት ዶክተር ስንታየሁ የወተት ተዋጽኦችን በተለያየ መንገድ አምርቶ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በግብርናና እንስሳት ኃብት ሚኒስቴር የወተት ኃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ተካ በበኩላቸው የወተት አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ የኀብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው በስፋት ቢሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ጠቁመዋል። የግብርናና እንስሳት ኃብት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንዳሉት፤ የወተት አቅርቦትን ለማሻሻል ውኃና ኤሌክትሪክ የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች መጠናከር አለባቸው። የመኖ አቅርቦት፣ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ማጠናከርና ጥራትን መሰረት ያደረገ የግብይት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን በሁለተኛው የእድገትና ትራንፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ለወተት የተመረጡ የእንስሳት ዝርያዎችን ለማሻሻል በዚህ ዓመት ፖሊሲ መጽደቁን ተናግረዋል። በፖሊሲው መሰረት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት ግንባታ እየተካሄደ እንደሆነም ገልጸዋል። የወተት ጥራትን ለማስጠበቅ ከምርት ጀምሮ የእንስሳት መኖ፣ የጤና ክብካቤ፣ የወተት መያዣ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ የመገልገያ እቃዎችን መጠቀም አስገዳኝ የሚሆንበት የአሰራረር ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን አስረድተዋል። በዓለም ላይ ስድስት ሚሊዮን ህዝብ ወተትና የወተት ተዋጽኦ ተጠቃሚ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ከፍተኛ የወተት እጥረት እንዳለ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎቸ በመግለፅ ላይ ናቸው። ዓለም አቀፉ የወተት ቀን በኢትዮጵያ ሲከበር ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም