ቀጥታ፡

የህዝብና ቤት ቆጠራ ሰልጣኞች ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል አቅም ገንብተናል አሉ

አዲስ አበባ  መጋቢት 7/2011 አራተኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ለማካሄድ በተሰጠው ስልጠና አገራዊ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት የሚያስችል አቅም ገንብተናን ሲሉ በአዲስ አበባ የአሰልጣኞች ስልጠና የወሰዱ የቆጠራ ተቆጣጣሪዎችና አሰልጣኞች ተናገሩ።

ቆጠራውን ቴክኖሎጂን በመጠቀም በግልጽና በቀላል መንገድ ለማካሄድ የሚያስችል ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታውቋል።

ባለፉት 14 ቀናት በከተማው ለሚካሄደው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በቴክኖሎጂና በተግባር የተደገፈ የአሰልጣኞች ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው።

ስልጠናውን የወሰዱ ተቆጣጣሪዎች እንደሚሉት የቆጠራው መረጃ ለትውልድ የሚተርፍ ተግባርን ለማከናወን ወሳኝ ሚና ስለሚኖረው አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በበቂ ሁኔታ ዝግጁ ሆነናል ብለዋል።

የተሰጣቸውም ስልጠና የቆጠራውን ጠቀሜታ በአግባቡ ተረድተው ቆጣሪዎች አገራዊ ዓላማን እንዲሰንቁ ለማድረግና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ተግባር ለማከናወን እንዲችሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በቆጠራው ወቅት ከህብረተሰቡ የሚፈለገው መረጃ ለመውሰድ የሚሞላው ቅጽ ሰፊ ቢሆንም እንዴት በቀላል ዘዴ ከህብረተሰቡ ጋር ተግባብቶ ለማፋጠን የሚረዳ እውቀት አግኘተናል ነው ያሉት።

ወጣት ተስፋ ደስታ  ለቆጠራው  በበቂ ሁኔታ ዝግጁ መሆኗንና የተሰጣትን ኢትዮጵያዊ ግዳች በኀላፊነትና በተጠያቂነት በታማኝነት  እንደምትፈጽም አስታውቃለች

''ያገኘነው ስልጠና ቀድሞ ከገመትነው የተሻለና ለአገር ወሳኝ ቆጠራ መሆኑን የተገነዘብኩበት ሂደት ነው ያለው። በቆጠራው ስልጠና ወቅት ወደ ስራ ስንገባ ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለው የተገመቱ ጉዳዮች ጥያቄዎች ተነስተው ከአሰልጣኞችም ከሰልጣኞችም ተነስተው በተብላላ መልኩ ገንዘቤ እንድንይዝ ተደርጓል።'' ያሉት ወይዘሮ ኢራባ አለማየሁ ናቸው፡፡  

ተቆጣጣሪዎቹ እንደሚሉት በቆጠራው ወቅት የንብረት መዘረፍና ቆጠራውን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ችግሮች እንዳይገጥሙ መንግስት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ አለበት።

ቆጠራውን ለማካሄድ የሚመደቡ ሰዎች ትክክለኛውን መስፈርትና በቂ እውቀት ያላቸው መሆኑን የሚመለከታችው አካላት በአግባቡ መከታተል እንዳለባቸው ተቆጣጣሪዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የቆጠራው ፎርም ሰፊ ጊዜና ትዕግስትን የሚጠይቅ በመሆኑ ቆጣሪዎች በትዕግስትና ህብረተሰቡን በማሳመን የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የተሰጣቸው ስልጠና ያግዛቸዋል ብለዋል።

የኤጀንሲው ከፍተኛ ባለሙያና የአዲስ አበባ ህዝብና ቤት ቆጠራ የቴክኒክ አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ኃይሉ እንዳሉት መንግስት የቆጠራው ዓላማ እንዲሳካና ከተቆጣሪዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሊያሳልጥ የሚችል ስልጠና ተሰጥቷል።

ቆጠራው ቴክኖሎጂን የሚጠይቅ በመሆኑ ሰልጣኞች በቂ ጊዜ ወስደው እንዲሰለጥኑ የተደረገ ሲሆን ተግባር ተኮር ስልጠና እንዲሰጣቸው ይደረጋል ነው ያሉት።

አሰልጣኞችም አብዛኞቹ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች ሲሆኑ ከህብረተሰቡ ጋር በቀላል ሊግባቡ የሚችሉና የተሻለ ለማህበረሱ የቀረቡ እንዲሆኑ መስፈርት ተዘጋጅቶ ተመልምለዋል።

እስካሁን 440 አሰልጣኖች ተመለምለው ስልጠና ያገኙ ሲሆን በቀጣይ ከ4 ሺህ 600 በላይ ቆጣሪዎች በ10ሩ ከፍለከተሞች ስልጠና ይሰጣቸዋል።

በቆጠራው ሂደት የጸጥታ ችግር እንዳይገጠማቸው አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ቆጠራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ነዋሪዎች ቆጣሪዎችን በማገዝና አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በመላው አገሪቱ የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንደሚጀመር ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም