ኢትዮጵያ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ቅርሶቿን ብዛትና ዓይነት መረጃ ማሰባሰብ ጀመረች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ቅርሶቿን ብዛትና ዓይነት መረጃ ማሰባሰብ ጀመረች
መጋቢት 7/2011 ኢትዮጵያ በተለያየ አጋጣሚ ከሀገር የወጡ ቅርሶቿ የሚገኙባቸውን ሀገራት፣ የቅርሶቿን ዓይነትና ብዛት መረጃ ማሰባሰብ መጀመሯን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።
በባለስልጣኑ የቅርስ ምዝገባና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው፤ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሀገር በመሆኗ በርካታ ተንቀሳቃሽና ቋሚ ቅርሶች ቢኖራትም ብዙ ቅርሶቿ በተለያየ አጋጣሚ ከሀገር መውጣታቸውን ገልጸዋል።
በቅኝ ግዛትና በወረራ ዘመን ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ብዙ ቅርስ ተወስዶባቸዋል፤ ኢትዮጵያም በጦርነት፣ በአሳሾች፣ በጎብኝዎች፣ በተመራማሪዎች የተለያዩ መሪዎች በስጦታና በስርቆት ብዙ ቅርሶች ወደ ውጭ ተወስደውባታል ነው ያሉት።
በተለይ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት በናፒየር ዘመቻ ወቅት እንግሊዞች በ15 ዝሆንና በ200 በቅሎ ብዙ ቅርስ ዘርፈው መሄዳቸውን አንስተዋል።
በተለያየ ምክንያት የተወሰዱት የኢትዮጵያ ቅርሶች በአውሮፓ፣ በእስያና በአሜሪካ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ደሳለኝ ፤ በተለይ የት ሙዚየም ወይም በማን ግለሰብ እጅ አሉ የሚለው በግልጽ እንደማይታወቅ ነው የጠቆሙት።
የቅርስ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኢዮብ ዋቅቶላ በበኩላቸው ቅርሶቹን ለማስመለስ ምን ያህል ቅርሶች በየትኛው ሀገር ይገኛሉ የሚለውን ትክክለኛ መረጃ የማሰባሰብ ስራ በዚህ ዓመት ለማጠናቅቅ መታቀዱንም ጠቁመዋል።
በየሀገራቱ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች፣ ከኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያ ወዳጅ ታዋቂ ሰዎች ጋር በመሆን ቅርሶችን ለመለየት መረጃ እያሰባሳብን ነው ብለዋል።
እንግሊዝ ውስጥ ያሉትን ቅርሶች የመለየትና የመመዝገብ ሥራ አፍሮሜት ከተባለው ኮሚቴ ጋር እየተሰራ ሲሆን ፈረንሳይ ውስጥ በዣክ ሺራክ ሙዚየም ብቻ 3 ሺህ 81 የኢትዮጵያ ቅረሶች መኖራቸውን መረጃ አግኝተናል ነው ያሉት።
በፈረንሳይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ዝርዝር ለመለየትም ሙዚየሙ የማውጫ መረጃውን እንዲሰጣቸው አዲስ አበባ የሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ በደብዳቤ መጠየቁን ጠቁመዋል።
የፈረንሳይ መንግስት የአፍሪካ ቅርሶች እንዲመለሱ አቋም በማሳየቱ የኤምባሲውን በጎ ምላሽ እየጠበቁ መሆኑን ነው ያነሱት።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው እንግሊዝ ውስጥ ከ1 ሺህ 400 በላይ ቅርሶች መኖራቸውን መረጃ መገኘቱን ተናግረዋል።
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ እንዲያሰባስብ አደራ ተጥሎበት በፅሁፍ መረጃዎችን እየሰበሰበ ነው ብለዋል።
ቅርሶችን ለማስመለስም ሆነ ለመለየት ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ያነሱት አቶ ገዛኸኝ ለዚህ ሥራ ስኬት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በቅርቡ በብሪታኒያ የጦር ሙዚየም የሚገኘውን የአፀ ቴዎድሮስን ጸጉር ለመመለስ መወሰኑ የዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ ማሳያ ነው ብለዋል።