የአውሮፕላን አደጋው የብዙ ሀገራት ዜጎችን ቢጎዳም ዓለምን የበለጠ አስተሳስሯል- ኢማኑኤል ማክሮን

92

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 ባለፈው ሳምንት የደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የብዙ ሀገራት ዜጎችን ቢጎዳም ዓለምን የበለጠ አስተሳስሯል ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት ኢማኑዬል ይህን ያሉት በናይሮቢ ውስጥ “አንድ ዓለም” (“One Planet”) በሚል ርዕስ በአፍሪካ አህጉር ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ባለውና የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እየተሳተፉበት ባለው ጉባኤ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡

ይህ አሳዛኝ አደጋ የዓለም ሀገራትን "በዚህ ፈታኝ ወቅት እንደ አንድ ቤተሰብ እንዲቆሙ አድርጓቸዋልም" ብለዋል።

የጉባኤው አስተባባሪና የመድረኩ መሪ ዘይን ቭርዬ ፕሬዚዳንት ማክሮን በቅርቡ ከኢትዮጵያ ከሰው ዘር መገኛ ምድር ይፋዊ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ኬንያ መምጣታቸውን በመጥቀስ እንኳን በሠላም መጡ ብለዋቸዋል።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች፥ ጓደኞችና የሥራ ባልደረቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።

በፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ጠያቂነትም ለተጎጂዎቹ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስትም መፅናናትን ተመኝተዋል።

በዚህ ጉባኤ ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ፥ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር በሆኑት በፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ተወክላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም