የመቀለ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በጅቡቲ ጉብኝት አደረጉ

99

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 የመቀለ ዩኒቨርሲቲ የሎጅስቲክስና አቅርቦት አስተዳደር ተመራቂ ተማሪዎች ጅቡቲን ጎበኙ፡፡

ጉብኝቱ ጅቡቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል የተመቻቸላቸው ሲሆን መቀለ ዩኒቨርሲቲ እና 'Kuhne-Stiftung Foundation' ዋና አዘጋጆች ናቸው፡፡

የተመራቂ ተማሪዎቹ ቡድን የጅቡቲ ወደቦችና ነጻ ቀጠና ባለስልጣን የጅቡቲ ወደቦችና ነጻ ቀጠናዎች ባለስልጣንን ጨምሮ ሌሎች ከሎጅስቲክስና አቅርቦት ጋር ተያያዥነት ያላቸው የጅቡቲና የኢትዮጵያ መንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በዚህ ሳምንት ጎብኝተዋል፡፡

በፕሮፌሰር አደም መሃመድ ሃቢብ የተመራው የኢትዮጵያውኑ ቡድን ከጅቡቲ የዶራሌ ኮንቴነር ተርሚናል የንግድ ዳይሬክተር ከሆኑት ሚስተር ዋርሳማ ሐሰን  እንዲሁም ከሆራይዘን የነዳጅ-ዘይት ተርሚናል ዋና አስተዳዳሪ ሆውሲን አህመድ ሆውሲን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ተማሪዎቹ ከ90 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ የገቢና የወጪ ምርቶች በሚተላለፉበት የጅቡቲ ኮሪደር የሎጅስቲክስና የአቅርቦት አሰራር፣ ከመነሻው ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ያለውን የኮንቴነር እንቅስቃሴ እንዲሁም የሎጅስቲክስ ፍሰትን ለማጠናከር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም ነው የጎበኙት፡፡

በሶስት ቀናት ቆይታቸው የኢትዮጵያ መርከቦች አጠቃላይ እንቅስቃሴን በተመለከተ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የጅቡቲና የኢትዮጵያ መንግስት ተቋማትም ተግባራዊ ስልጠና መውሰዳቸውንም በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ዳያስፖራ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ጉብኝቱ የሁለቱን አገራት ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ይበልጥ ሊያሳድጉ የሚችሉ ናቸውም ተብሏል፡፡

በአህጉሪቱ ተምሳሌታዊ የሆነውን ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከርም የሁለቱ አገራት መንግስታት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም