ቀጥታ፡

የጎንደር የእንስሳት አድላቢዎችና የወተት ላም አርቢዎች በቃጠሎ ከደረሰባቸው ጉዳት ማገገም አልቻልንም አሉ

ጎንደር መጋቢት 4/2011 በጎንደር ከተማ በአዘዞ አካባቢ ንብረታቸውን ያጡ የእንስሳት አድላቢዎችና የወተት ላም አርቢዎች በቃጠሎ ከደረሰባቸው ጉዳት ማገገም እንዳልቻሉ ገለጹ።

ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን በከተማው የአዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ አስታውቋል፡፡

የእንስሳት አድላቢዎችና የወተት ላም አርቢዎቹ ለኢ ዜ አ እንዳሉት በአደጋው ንብረታቸውን በማጣታቸው ተቸግረዋል።

በወተት ላሞች እርባታ የተሰማሩት አቶ ደርጉ አበበ በቃጠሎው አራት የወተት ላሞችና ሁለት ጥጆችን ማጣታቸውን ተናግረዋል።

"ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም/አብቁተ/ የተበደርኩትን 300 ሺህ  ብር ለመክፈል ከማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ" ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት  ተከራይተው ለሚኖሩበት መኖሪያ ቤት  ወርሃዊ ኪራይ ለመክፈል እንደተቸገረ የገለጹት አቶ ደርጉ፣በጉዳቱ  አምስት  ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር እንዳልቻሉ አመልክተዋል።

ሌላው በቃጠሎ ንብረቱን ያጡት አቶ አሰፋ አቡሃይ ባቋቋሙት የእንስሳት ማድለቢያ ሥራ የተፈጠረላቸው 10 ሰዎች ሥራ አጥ ለመሆን መገደዳቸውን ተናግረዋል።

በቃጠሎው ግምቱ ከ400 ሺህ ብር በላይ የሆነ የከብቶች መጠለያ የእንስሳት መኖናና ሁለት የደለቡ ሰንጋዎችን አጥቻለሁ ብለዋል።

የአዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለበል ዓለሙ ክፍለ ከተማው ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተደረገ ባለው ጥረት ያቋቋመው ግብረ ኃይል ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ክፍለ ከተማው የቃጠሎውን ቦታ ከማጽዳት ጀምሮ የጉዳቱን መጠን መለየቱን አመልክተው፣ ተጎጂዎች ተጨማሪ የግንባታ ቦታ የሚያስፈልጋቸው ከሆነም፤ በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

የግብረ ኃይሉ አስተባባሪ መቶ አለቃ ሙላት ከበደ ተጎጂዎችን በአጭር ጊዜ ለማቋቋም በተደረገው ጥረት ከ200 ሺህ ብር በላይ ከኅብረተሰቡ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

በተጎጂዎቹ ላይ የደረሰው የንብረት ጉዳት ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው፣ ከዚህ አንጻር የኅብረተሰቡና የመንግሥት ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል፡፡

ጥር 29/2011በከተማው ልዩ ስሙ ግራር ሰፈር በተባለው አካባቢ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ በአምስት ማህበራት የተደራጁ 20 ግለሰቦች ንብረት ወድሟል።

በአደጋው 51 የወተት ላሞችና የደለቡ ሰንጋዎችን ጨምሮ 20 የእንስሳት መጠለያ ክፍሎችና የእንስሳት መኖ መቃጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም