በሆርቲፍሎራ ዘርፍ የሚታዩ የፖሊሲና የቢሮክራሲ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መሄድ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
በሆርቲፍሎራ ዘርፍ የሚታዩ የፖሊሲና የቢሮክራሲ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መሄድ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ መጋቢት 4/2011 መንግስት በሆርቲፍሎራ ዘርፍ የሚታዩ የፖሊሲና የቢሮክራሲ ተግዳሮቶችን ለመፍታተ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
ሰባተኛው ዓለም አቀፉ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አውደ-ርዕይ "መጪው ዘመን የሆርቲካልቸር ነው" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በዛሬው እለት ተከፍቷል።
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ዘርፉ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ እያደገ ያለውን ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው ነው።
አዳዲስ ስራዎችን ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት፣ የተማረውንና ያልተማረውን፣ ክህሎት ያለውንና የሌላቸውን በተለይም ሴቶችን በስራ ፈጠራ በከፍተኛ ደረጃ እየጠቀመ ይገኛልም ብለዋል።
በአገሪቷ የሚገኙትን ጥቃቅንነ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ብቻ ሳይሆን ለትላልቅ ኢንተርፕራይዞችም ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተናግረዋል ዘርፉ።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩት የአበባ ኢንቨስትመንቶች በብዛትና በስፋት ትልቅ መሻሻል እያሳዩ እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቷ፤ እስካሁን በዘርፉ የተገኙትን ስኬቶች አጠናክሮ ለመሄድ ተግዳሮቶችን መፍታት ተገቢ ነውም ብለዋል።
ለዚህም መንግስት በሆርቲፍሎራ ዘርፍ የሚታዩ የፖሊሲና የቢሮክራሲ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
ይህም በተለምዶ የሚሰራው የሆልቲካልቸር ሥራዎችን በማስቀረት አዲስና ስር-ነቀል የሆነ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ሲሉም አብራርተዋል።
የሆርቲካልቸር ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም እንዲቻል የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የግሉን ሴክተር ጨምሮ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ፕሬዝዳንቷ ጠይቀዋል።
ማህበራዊና አከባቢያዊ ኃላፊነትን መወጣት፣ የሰራተኞችን የስራ ደህንነት ማረጋገጥ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዳ ስልጠና መስጠት፣ በተለይም ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ጤናቸውንና የልጆቻቸው እንክብካቤ እንዲጠበቅ ማድረግ ከግሉ ዘርፍ ይጠበቃል ሲሉም ተናግረዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው በአገሪቷ በሆርቲካልቸር ያልተነካ እምቅ አቅም ያለ ሲሆን አቅሙን ለመጠቀም መንግስት በጀመረው ሪፎርም ለቢዝነስና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ እየሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም ሰላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ የሥራ ሁኔታን መፍጠር ለኢንቨስትመንቱ በተለይም በሆርቲካልቸር ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ ጠቅሰው፤ መንግስት ይህንኑ ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ እንደሆነም አክለዋል።
ነገር ግን ሰላምን ማስፈን ለመንግስት ብቻ የተተወ የአንድ ወገን ተግባር ሳይሆን ባለሃብቱ በሚሰማራበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከሰራተኛውና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በሚፈጥራቸው ቁርኝቶች የሚያሳካቸው ወሳኝ ተግባራት ናቸው ብለዋል።
ስለሆነም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ባለሃብቱና ህብረተሰቡ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዘላለም መሰለ በየዓመቱ የሚዘጋጀው አውደ-ርዕይ የኢንቨስትመንት እድሎችን ለማሳደግ እንዲሁም የቢዝነስ ሰዎችን እንዲገናኙና የእውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ እያገዘ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም አለም አቀፍ ምሁራንና ባለሙያዎችን በማገናኘት ዘርፉ ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን እያገለገለ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ምርቶች በአለም አቀፍ ገበያ በጥራትና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያስቻለ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በምርቶቹ የአመራረት ሂደት ወቅት በአካባቢና በሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይኖር አለም አቀፍ ደረጃን እንዲያሟሉና እውቅና እንዲሰጣቸውም እየተደረገ እንደሆነ ነው አቶ ዘላለም የተናገሩት።
በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ሴክተር ከመቶ ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል የተፈጠረላቸው ሲሆን 85 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
---END---