የአውሮፕላኑን አደጋ መንስዔ ለማወቅ መረጃ የማሰባሰቡ ስራ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፕላኑን አደጋ መንስዔ ለማወቅ መረጃ የማሰባሰቡ ስራ ቀጥሏል
አዲስ አበባ መጋቢት 4/2011 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ እያለ ባለፈው እሁድ አደጋ የገጠመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በተከሰከሰበት ስፍራ መረጃ የማሰባሰቡ ሂዳት እንደቀጠለ ነው።
በትራንፖርት ሚኒስቴር የአደጋ ምርመራ ቢሮ ኃላፊ አቶ አምድዬ አያሌው ለኢዜአ እንደገለፁት የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ የቴክኒክ ምርመራ ቡድን ተቋቁሞ መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛል።
የምርመራ ቡድኑ የአውሮፕላኑ አደጋ በተከሰተበት ስፍራ መረጃ የማሳባሰቡን ስራ አሁንም በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአሜሪካ የመጡ ባለሙያዎችም ለዚሁ የምርመራ ስራ የማማከር አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በቀጣይ ምርመራውን በጋራ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየመከሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ በረራ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃ በኋላ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ 157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የተከሰከሰው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ያጡ 35 የተለያዩ አገራት ዜጎች ይገኙበታል።