ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስና ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች በኡጋንዳ በተካሄዳው የምስራቅ አፍሪካ ዞን አምስት የታዳጊዎች እጅ ኳስ ውድድር በነበራቸው ተሳትፎና በመርሃ ግብሮች ላይ ማስተካከያ ማድረግ በማስፈለጉ ፕሪሚየር ሊጉ ላለፉት ሶስት ሳምንታት ተቋርጦ ነበር። በዚሁ መሰረት ቅዳሜ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ፌዴራል ፖሊስ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። በክልል ከተማ ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከቡታጅራ ከተማ ከረፉዱ አምስት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። እሁድ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከጠዋቱ 3 ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠኝ የእጅ ኳስ ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። በሌላ በኩል የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የቮሊቦል ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜና እሁድ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ። ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞች ሮቤ ላይ መዳወላቡ ዩኒቨርስቲ ከመከላከያ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ30 እንዲሁም ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ላይ የሚጫወቱ ይሆናል። እሁድ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ፌዴራል ማረሚያ ከጣና-ባህርዳር ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ላይ ይጫወታሉ። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች የቮሊቦል ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት መርሃ ግብርም ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ውሃ-ስራዎች ከጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ፕሪሚየር ሊጉን ውሃ ስራዎችና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በተመሳሳይ 12 ነጥብ ባሸነፉት የጨዋታ መጠን ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። ውሃ-ስራዎች የቅዳሜን ጨዋታ አሸንፎ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም በሚደረገው የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ከተሸነፈ ውሃ ስራዎች የሊጉ አሸናፊ ይሆናል። የጌታዘሩ ስፖርት ክለብም በሂሳባዊ ስሌት ዋንጫ የማግኘት እድሉ አልተሟጠጠም። በአንጻሩ ውሃ-ስራዎች ቢሸነፍና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የመጨረሻውን ጨዋታ ቢያሸንፍ ማረሚያ ቤቶች ሻምፒዮን መሆን ይችላል። የኢትዮጵያ ሴቶች የቮሊቦል ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አራት ቡድኖች የሚሳተፉበት ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም