ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን የጂቡቲ አቻውን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸነፈ

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2011 በምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን የጅቡቲ አቻውን 52 ለ 3 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።

የዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው ውድድር ዛሬ በዛንዚባር ተጀምሯል።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኡጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ብሩንዲ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ኬንያ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ ከ18 እና 20 ዓመት በታች በሁለት ብሔራዊ ቡድኖች ተወክላለች።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዛሬ በውድድሩ መክፈቻ ቀን የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን የጂቡቲ አቻውን 52 ለ 3 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።

ከ18 ዓመት በታች የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሁለት ከጅቡቲ፣ ብሩንዲና ሩዋንዳ ጋር እንደተደለደሉና ሁለተኛ ጨዋታቸውን ነገ ከብሩንዲ ጋር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። 

''ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ በምድብ አንድ ከኬንያ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ መደልደላቸውን ገልጸው ከነገ በስቲያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር ያደርጋሉ'' ብለዋል።

27 ተጫዋቾችን ጨምሮ 33 ልዑካንን የያዘው ብሔራዊ ቡድኑ ትናንት ወደ ስፍራው ማቅናቱ ይታወሳል።

የምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር እስከ መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በ2007 እና በ2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በ2009 ዓ.ም በጂቡቲ አዘጋጅነት በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም