ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አቀባበል አደረጉ

አዲስ አበባ  መጋቢት 3/2011 ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በላሊበላ  አየር ማረፊያ ተገኝተው ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን  አቀባበል አደረጉላቸው።

በአቀባበል ስነ ስርዓት ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።  

ለፕሬዚዳንት ማክሮን ክብር ሲባልም ዘጠኝ ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን የላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናትን እንደሚገበኙ ይጠበቃል።

የፕሬዚዳንቱ የላሊበላ ጉብኝት ዓላማ ቅርሱ በአሁኑ ወቅት ያለበትን ጉዳትና ቅርሱን ከጥፋት ለመታደግ የፈረንሳይ መንግስት ሊያደርግ የሚገባውን ድጋፍ ለማጤን መሆኑም ተገልጿል። 

ባለፈው ጥቅምት ወር ጠቅላይ ሚንስትር ዶከተር አብይ በፈረንሳይ ባደረጉት ጉብኝት ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

በውይይቱ ወቅትም  ፈረንሳይ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተጋረጠውን ችግር ለመፍታት ድጋፍ  እንደምታደርግም ፕሬዝዳንቱ ቃል ገብተው ነበር።

የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ደርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የቅርስ ኃብቶችን በአግባቡ ጠብቆ ለማቆየት ሊደረግ በሚገባው ክብካቤ ላይ ያተኮረ ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል ይፈረማል። 

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ የፈረንሳይ ቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ወደላሊበላ በመጓዝ የቅርሱን ሁኔታ በተመለከተ ለሶስት ጊዜ ያህል ጥናት ማካሄዳቸውም ተነግሯል።

ከዚህም ሌላ የፈረንሳይ ባለኃብቶች መዋእለነዋያቸውን በኢትዮጵያ  በስፋት በማፍሰስ በአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ አንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉበትን መንገድ ለማመቻቸት የሚያስችል ስምምነትም በማክሮን ጉብኝት ወቅት ይፈረማል ተብሏል። 

በአሁኑ ወቅት 120 ያህል የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እየሰሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ንጉሱ ስምምነቱ ይህንን የፈረንሳይ ተሳትፎ የበለጠ ማጠናከር እንደሆነም አክለዋል።

የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይልን አቅም ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነትም በሁለቱ አገራት መካከል እንደሚፈረምም ታውቋል።  

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ቢሆንም መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት ግን በ1907 ነው።

የፕሬዚዳንቱ የሶሰት ቀናት ጉብኝት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የትበብር ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል መሰረት ይጥላል ተብሎ ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም