ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የጥጥ ልማት እየተዳከመ ነው....የዘርፉ ተመራማሪ

አዳማ መጋቢት 3/2011 ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት ምቹ የአየር ፀባይና ሰፊ መሬት ቢኖራትም ዘርፉ ትኩረት በማጣቱ ምክንያት ልማቱ እየተዳከመ መምጣቱን በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪና ባለሃብቶች ገለጹ።

ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ኢትዮጵያ በጥጥ ምርት ከዓለም የአራተኛ ደረጃን ከያዘችው ፓኪስታን ጋር የሚመጣጠን አመቺ የእርሻ መሬትና ተስማሚ የአየር ፀባይ ያላት አገር ብትሆንም ለዘርፉ ትከረት አልተሰጠውም።

በእዚህም የሚመረተው የጥጥ ምርት ሀገሪቱ ካላት እምቅ ሃብት ከ4 በመቶ ያነሰ መሆኑን ነው በወረር ግብርና ምርምር ማዕከል የብሔራዊ የጥጥ ማስተባበሪያ ተመራማሪ አቶ ዶኒስ ጉርሜሳ የገለጹት።

በብቸኝነት የጥጥ ምርምርን የሚያካሄደው የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ላለፉት 53 ዓመታት ባካሄደው ምርምር በሽታን የሚቋቋሙና የተሻለ ምርት የሚሰጡ 35 የጥጥ ዝርያዎችን ቢያወጣም ለአምራቾች አባዝቶ የሚያከፋፍል አካል ባለመኖሩ በሚፈለገው ልክ ተደራሽ አለመሆኑን ተመራማሪው ተናግረዋል ።

አቶ ዶኒስ እንዳሉት በ2008 ዓ.ም ብቻ በሄክታር ከ39 እስከ 46 ኩንታል ድረስ ምርት የሚሰጡ ወረር 50፣ ወይጦ 07 እና ሲሲ ኩክ 02 የተባሉ ምርጥ የጥጥ ዝርያዎች ፀድቀው ቢወጡም በሚፈለገው ፍጥነትና መጠን ወደ አምራቹ እየደረሱ አይደለም።

እንደአቶ ዶኒስ ገለጻ የጥጥ ልማቱን በበቃት ማከናወን ያልተቻለው በአገር አቀፍ ደረጃ ምርምሩን የሚያስተባብረው አካል ትኩረት ባለማግኘቱ ነው።

ማዕከሉ ለልማቱ የራሱ የሆነ የሰርቶ ማሳያ መሬትም ሆነ ላቦራቶሪ የሌለው መሆኑና በአቅም ግንባታ በኩል ትኩረት አለመሰጠቱ ስራውን በብቃት ለማከናወን እንቅፋት እንደሆነበትም አመልክተዋል።

ለአንዳንድ የጥጥ ምርምሮች የምርምር ማዕከሉ ናሙና ቃሊቲ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ላቦራቶሪ በመውሰድ ከመስራት የዘለለ ተግባር ማከናወን እንዳልቻለም ከተመራማሪው ገለጻ ማወቅ ተችሏል።

በመካከለኛው አዋሽ አካባቢ 120 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ ሰብል ሲለማ እንደነበር የገለጹት ተመራማሪው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አምራቾች በቂ ትኩረትና እገዛ ባለማግኘታቸው የጥጥ መሬታቸውን ወደ ሸንኮራ አገዳና ሙዝ እየቀየሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

" በአሁኑ ወቅትም በጥጥ የሚለማው መሬት ከ70 ሺህ ሄክታር አይበልጥም " ብለዋል።

በአካባቢው 1 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በጥጥ ልማት እያለሙ የሚገኙት ባለሃብት አቶ አህመድ መሃመድ በበኩላቸው ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት አለመሰጠቱ ከ40 ዓመት በፊት የተለቀቀና ምርታማነቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣ የጥጥ ዝርያ እንዲጠቀሙ ያደረጋቸው መሆኑ ገልጸዋል።

ነባሮቹ የጥጥ ዝርያዎች አቅማቸው እየተዳከመ በመምጣቱ ምርታማነታቸው ከነበረበት ከ60 እና 50 ኩንታል በሄክታር በአሁኑ ወቅት ወደ 34 ኩንታል ዝቅ ማለቱንም አስረድተዋል።

በአካባቢው የነበረው የመንግስት የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ በመበላሸቱ ምክንያት ያመረቱት የጥጥ ክምችት ለብልሽት እየተዳረገባቸው መሆኑንም ባለሀብቱ ገልፀዋል።

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከልም ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ የሚሄድ ምርምር በማካሄድ እንዲያግዛቸውም ጠይቀዋል።

"የጥጥ ምርት በተባይና በአረም በቀላሉ የሚጎዳ ሰብል በመሆኑ ተገቢውን ፀረ አረም ኬሚካል በወቅቱ የምናገኝበትና የጥጥ ማዳመጫ ፋብሪካ በአካባቢው መገንባት የምንችልበት ሁኔታ በመንግስት እንዲመቻች እንፈልጋለን" ብለዋል።

በአሚባራ ወረዳ በ86 ሄክታር መሬት ጥጥ  በማልማት ላይ የሚገኙት ሌላው ባለሃብት አቶ ደምለው ገበየሁ በበኩላቸው የዘርፉ ዋነኛ ችግር የተሻሻለ ዘርና የፀረ ተባይ ኬሚካል አለማግኘት መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ አንድ ዓይነት የጥጥ ዝርያ ብቻ እንደሚቀርብላቸው የገለጹት ባለሀብቱ ዝርያው ከአካባቢው ጋር በመላመዱ በሄክታር የሚሰጠው ምርት ከ40 ኩንታል ወደ 34 ኩንታል መቀነሱን አመልክተዋል።

የጥጥ ልማት እየተጠናከረ እንዲመጣም የተሻሻሉ የጥጥ ዝርያዎችንና በቂ ኬሚካል ለባለሀብቱና ለአር ሶአደሩ ሊቀርብ እንደሚገባ አቶ ደምለው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወረር  ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ መገርሳ ስለሁኔታው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ "በጥጥ አምራቾች በኩል የቀረበው ቅሬታ ትክክል ነው" ብለዋል።

የጥጥ ልማቱ አንዴ በግብርና ሚኒስቴር ሌላ ጊዜ ደግሞ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር እንዲተዳደር ሲደረግ መቆየቱና በእዚህም ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ባለቤት ያልነበረው መሆኑ ለችግሩ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።

"በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መስራች ዘሩን ከወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ወስዶ በአሶሳ አካባቢ የማባዘት ሥራ እያከናወነ በመሆኑ ችግሩ መፍትሔ ያገኛል" ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም