የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ተመራ - ኢዜአ አማርኛ
የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ተመራ
አዲስ አበባ መጋቢት 3/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መራ።
ምክር ቤቱ ለፌዴራል መንግስት የ2011 በጀት ዓመት የቀረበውን 33 ነጥብ 99 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በዝርዝር እንዲታይ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
ዛሬ በተካሄደው 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 26ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ አዋጆችና የብድር ስምምነቶች ላይ ውይይት ተደርጎ ወደሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ተልኳል።
የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 1540/2004 መሰረት የወጣ ረቂቅ እንደሆነ ተገልጿል።
የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍ ዓለም አቀፍ የደህንነት ስጋት በመሆኑ ከሌሎች አገሮች ጋር ለመከላከል፣ ለመግታትና ለመቆጣጠር በትብብር ማዕቀፍ ለመስራት ያግዛል።
ኢትዮጵያ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን ከመከላከልና መቆጣጠር ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ማጽደቋም ረቂቅ አዋጁን እንድታዘጋጅ ያስገድዳታል ተብሏል።
በዚህም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 38/2011 ለዝርዝር እይታ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
የፌዴራል መንግስት የ2011 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት ላይም ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር የቀጥታ የበጀት ድጋፍ በእርዳታና በብድር ለመደበኛ ወጪ 33 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ 240 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ጥቅም ላይ እንዲውል ቀርቧል።
ለ2011 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት በእርዳታ 16 ነጥብ 99 ቢሊዮን እንዲሁም በብድር 16 ነጥብ 99 ቢሊዮን ብር ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር የቀጥታ የበጀት ድጋፍ የተገኘ እንደሆነ ተገልጿል።
ነገር ግን ''ለመደበኛ ወጪ የምትበደረው ገንዘብ ከካፒታል ወጪ መብለጥ የለበትም'' ከሚለው የኢትዮጵያ የበጀት ፖሊሲ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲያየው የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ራሱን የቻለ የፌዴራል መስሪያ ቤት እንዲሆን የሚያስችል የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
አዋጁ መንግስት የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሪፎርም በጠንካራ ፖሊሲ ለመምራትና በተሟላ ቁጥጥር ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል ያግዘዋል ተብሏል።
በኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች በግል ባለሃብቶች ተሳትፎና በውድድር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከማስቻሉም ባለፈ ነጻና ገለልተኛ የቁጥጥር መስሪያ ቤት እንዲኖር ያደርጋልም ተብሏል።
የምክር ቤቱ አባላትም ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለየሰው ሃብት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።