ቀጥታ፡

የኤሌትሪክና የውኃ አገልግሎት ማግኘት ለይዞታ ማረጋገጫነት ዋስትና አይሆንም---ተቋማት

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2011የኤሌትሪክና የመጠጥ ውኃ ተጠቃሚ መሆን ለህገ ወጥ ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ እንደማይሆኑ ኀብረተሰቡ ሊገነዘበው እንደሚገባ የተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

ኀብረተሰቡ በህገ ወጥ መንገድ፣ በግዢም ሆነ በወረራ የሚይዛቸው ቦታዎች ባለቤት ያላቸው መሆናቸውን በመገንዘብ ከእንደዚህ ዓይነት ተግባር እንዲቆጠቡ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ይዞታ አስተዳደር አሳስቧል።

በተለያየ ጊዜ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ይዞታዎች ሲፈርሱ ነዋሪዎቹ እንደ ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫነት የሚያቀርቡት የኤሌትሪክና የመጠጥ ውኃ ተጠቃሚ የሆኑበትን ሰነድ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ እንዳሉት፤ ደንበኞች አገልግሎቱን በቋሚነትና በጊዜያዊነት እንዲያገኙ ይደረጋል።

የይዞታ ማረጋገጫን ጨምሮ ሌሎች ተገቢ ማስረጃዎች ያሏቸው ሰዎች በቋሚነት የኤሌክትሪክ ቆጣሪ የሚያገኙ ሲሆን በሚኖሩበት አካባቢ የነዋሪነት መታወቂያ ያላቸውና ሦስት ሰዎችን በምስክርነት ያመጡ ደንበኞች ደግሞ ጊዜያዊ አገልግሎት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

ጊዜያዊ የኤሌትሪክ አገልግሎት ለማግኘት የይዞታ ማረጋገጫ እንደማይጠየቅ የገለጹት አቶ መላኩ፤ ነዋሪዎቹ የሰፈሩበት ቦታ ለሌላ ጉዳይ ተፈልጎ በሚነሱበት ወቅት የኤሌትሪክ አገልግሎቱ እንደሚቋረጥ የሚገልጽ ውል አስቀድሞ ከደንበኞች ጋር እንደሚፈጸም ተናግረዋል።

ኀብረተሰቡ የኤሌትሪክ አገልግሎትን እንዲያገኝ የሚደረገው በአሁኑ ወቅት ኤሌክትሪክ መሠረታዊ ፍላጎት እየሆነ በመምጣቱ መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ ኀብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘቱን እንደ ይዞታ ማረጋገጫነት አድርጎ ሊወስደው እንደማይገባም አሳስበዋል።  

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞች አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አርጋው በበኩላቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሌላቸው ደንበኞች ባለስልጣኑ የሚሰጠውን አገልግሎት ማግኘት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

እንዲሁም አገልግሎት ፈላጊዎቹ የሚኖሩበት ቤት የቀበሌ ከሆነ እንደሚስተናገዱ የገለጹት አቶ ሞገስ የግል ቤት ሰርተው የይዞታ ማረጋገጫ ለማግኘት እየተጠባበቁ ያሉ ሰዎች ከሚመለከተው የመንግስት አካል ማረጋገጫ ሲያቀርቡ አገልግሎቱን ያገኛሉ ብለዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው አስተዳደር ማረጋገጫ ካመጡና ሌሎች የሚያስፈልጉ ነገሮችን ያሟሉ ሰዎች የቦኖ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም  አስረድተዋል።

ኀብረተሰቡ ለሚያገኘው አገልግሎት ህጋዊ መንገድ መከተል እንዳለበት የጠቆሙት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጁ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም በህግ አግባብ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ቢቂላ በበኩላቸው አስተዳደሩ እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ በከተማዋ ውስጥ አግባብ ባላቸው አካላት ሳይፈቀድ የተያዙና ሰነድ አልባ የሆኑ ይዞታዎችን ወደ ህጋዊ የማምጣት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በህገ ወጥ መንገድ በብዛት የሚገነቡ ቤቶች በአገሪቱ የፀጥታ ችግር በሚኖርበት ወቅትና በሌሊት በመሆኑ ለቁጥጥር አዳጋች እንደሆነም ተናግረዋል።

ህገ ወጥ ይዞታዎችን ለማፍረስ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት ነዋሪዎች የፍርድ ቤት እግድ በማውጣት አስተዳደሩ የጀመረው ህገ ወጥ ተግባራትን የማስቆም ስራ እንዲጓተት እያደረጉ መሆኑንም አስረድተዋል።

ኀብረተሰቡ ባዶ የሚባል ቦታ አለመኖሩን በመገንዘብ ህገ ወጥ ይዞታን በግዢም ሆነ በወረራ ከመያዝ መቆጠብ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም