በአውሮፕላኑ አደጋ ዙሪያ ለተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ገለፃ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአውሮፕላኑ አደጋ ዙሪያ ለተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ገለፃ ተደረገ
አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር በትናንትናው እለት በተከሰከሰው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ያጡ 35 የተለያዩ አገራት ዜጎች ይገኙበታል።
በደረሰው አደጋም 149 መንገደኞችንና ስምንት የበረራ አስተናጋጆችን ጨምሮ በድምሩ የ157 ሰዎች ህይወት አልፏል።
ይህንን ተከትሎም የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአደጋው ዜጎቻቸውን ያጡ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችን በመጥራት ገለፃ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ አገልግሎቶች ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ወልደማሪያም ባደረጉት ገለፃም የአየር መንገዱ አውሮፕላኖች በታሪክ አጋጣሚ እንደዚህ አይነቱ መሰል አደጋ አስተናግደው አያውቁም።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ከተረከበው አራት ወር የሆነው ቦይንግ 737 ወደ ኬንያ የሚያደርገወን ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ከጆሃንስበረግ ደቡብ አፍሪካ ተመልሶ ለሶስት ሰዓታት ያህል ማረፉን አብራርተዋል።
አውሮፕላኑ ቀደም ብሎ በተካሄደ የቴክኒክ ፍተሻ ምንም ዓይነት ችግር ያልነበረበት መሆኑንም ለየአገራቱ አምባሳደሮች አስረድተዋቸዋል።
የአውሮፕላኑ የአደጋ መንሰኤ አለማቀፍ የአቬሽን ሕግን በተከተለ መልኩ ዓለም አቀፍ ምርመራ ተካሂዶ ዝርዝር መረጃው ወደ ፊት እንደሚገለጽም አስረድተዋቸዋል።
በአዳጋው ህይወታቸውን ያጡ የውጪ አገራት ዜጎች ወዳጅ ዘመዶቻቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሚፈልጉትን መረጃ ለማግኘት ነፃ የአየር ትኬትን ጨምሮ የሆቴልና ሌሎች ወጪዎችን አየር መንገዱ እንደሚሸፍንም አረጋግጠዋል።