ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ቡድን በዞን አምስት የእጅ ኳስ ውድድር ለመሳተፍ ወደ ዛንዚባር አቀና

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011 የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የእጅ ኳስ ውድድር ለመሳተፍ ዛሬ ወደ ዛንዚባር አቀና።

የዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው ውድድር ነገ ይጀመራል።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኡጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ብሩንዲ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ኬንያ ይሳተፋሉ።

ኢትዮጵያ ከ18 እና 20 ዓመት በታች በሁለት ብሔራዊ ቡድኖች ትወከላለች።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ 27 ተጫዋቾችን ጨምሮ 31 ልዑካንን የያዘው ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ ስፍራው ማቅናቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ትናንት ማምሻውንም ለልዑካን ቡድኑ የተዘጋጀ የአሸኛኘት ስነ-ስርዓት እንደተካሄደም አመልክተዋል።

ከ18 ዓመት በታች የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሁለት ከጅቡቲ፣ ብሩንዲና ሩዋንዳ ጋር የተደለደለ ሲሆን ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ በምድብ አንድ ከኬንያ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ መደልደላቸውንም አመልክተዋል።

ነገ በውድድሩ መክፈቻ ቀን ከ18 ዓመት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከጅቡቲ ጨዋታውን የሚያደርጉ ሲሆን ከነገ በስቲያ ደግሞ ከብሩንዲ አቻቸው ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።

ከነገ በስቲያ ከ20 ዓመት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን መጋቢት 4 ቀን 2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር ያደርጋሉ።

ደረጀ ታደገና ፍቅርተ ታደለ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን እንዲሁም መሐመድ አህመድና ቤተልሄም ረጋሳ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን በቅደም ተከተል በዋናና በምክትል አሰልጣኝነት ይመራሉ።

የምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር እስከ መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በ2007 እና በ2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በ2009 ዓ.ም በጅቡቲ አዘጋጅነት በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም