ማህበሩ ለህዝብና ቤቶች ቆጠራ ስኬታማነት የድርሻውን እንደሚወጣ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ለህዝብና ቤቶች ቆጠራ ስኬታማነት የድርሻውን እንደሚወጣ አስታወቀ
ባህርዳር መጋቢት 2/2011 በህዝብና ቤቶች ቆጠራ ለሀገሪቱ ቀጣይ ዕድገት የሚበጁ ትክክለኛ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የድርሻቸውን እንደሚወጣ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር አባላት ተናገሩ።
ማህበሩ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን 28ኛ ዓመታዊ ጉባኤ አጠናቋል።
የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስታቲስቲክስ ትምህርት ክፍል ዲን ዶክተር ሽብሩ ተመስገን ለኢዜአ እንደገለጹት በቆጠራው የሚሰበሰብ ትክክለኛ መረጃ ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ድርሻ አለው።
በተያዘው ወር መጨረሻ ለሚጀመረው 4ኛው ዙር የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የሚሰበሰበው መረጃ ለሀገር ዕድገት ጠቃሚ መሆኑን በመረዳት ሁሉም ሰው ለቆጣሪዎች ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጥ አስገንዝበዋል።
ማህበሩ መረጃ ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ እንዲሰበሰብና ጥራት ያለው መረጃ ለሕብረተሰቡ እንዲደርስ በዋናነት ስለጠቀሜታው የማስተዋወቅ ሥራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
"ያለመረጃ ሀገር ሊገነባ አይችልም " ያሉት ዶክተር ሽብሩ የትምህርት፣ የጤና፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና ሌሎች ተቋማትን ለመገንባትና ለማስፋፋት ትክክለኛ መረጃ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የማህበሩ አባላት ቆጠራውን ገለልተኛ ሆነው በመታዘብ በየአከባቢው የሚታዩ ግድፈቶችን ለሚመለከተው አካል ፈጥነው በመጠቆም እንዲታረሙ ለማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
" በቆጠራ ወቅት ሕብረተሰቡ የሚሰጠው መረጃ የተሳሳተ እንዳይሆንና መረጃውን የሚሰበስቡ ሰዎችም የተሳሳተ መረጃ እንዳያቀርቡ ሙያዊ ግዴታዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
ሌላኛው የማህበሩ አባልና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስታቲስቲክስ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው እንዳሉት የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ለውሳኔ የሚያግዙና ልማትን ለማፋጠን የሚያስችሉ መረጃዎች ለመሰብሰብ ያስችላል።
"መረጃዎች በአግባቡ ካልተሰበሰቡ ለፖሊሲ አውጪዎች የሚተላለፈው መልዕክት የተዛባ ሊሆን ይችላል" ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በትክክል ባልተሰበሰበ መረጃ ላይ ተነስቶ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ከዕውነታው የራቁ ስለሚሆኑ የህዝብና ቤት ቆጠራው በተያዘለት ጊዜና ወቅት በአግባቡ እንዲከናወን የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ከማህበሩ በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሰረትና ሙያዊ በሚጠይቀው መሰረት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ ስለህዝብና ቤት ቆጠራው ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለቆጠራው አስፈላጊነትና ፋይዳ ትምህርት እየሰጡ መሆኑን ዶክተር አስራት ገልጸዋል።
ቆጠራው ሀገሪቱ ለቀጣይ 10 ዓመታት የምትመራበት መረጃ የሚሰበሰብበት በመሆኑ ለዚህ ሁሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባልና በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዘይቱ ጋሸ ናቸው።
ከቆጠራው በፊት፣ በቆጠራው ወቅትና ከቆጠራው በኋላ የቆጠራውን ሂደት ተከታትለው በመታዘብ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር "ጥራት ያለው መረጃ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ዕድገት " በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀናት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያካሄደው 28ኛ ዓመታዊ ጉባኤ ተጠናቋል።