ቀጥታ፡

ዓለም-ዓቀፍ የአበባ ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ አውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011 ዓለም-ዓቀፍ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ በመጪው ረቡዕ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከፈታል፡፡

"መጪው ዘመን የሆርቲካልቸር ነው" በሚል መሪ ቃል ለሶስት ቀናት በሚካሄደው አውደ-ርዕይ በአበባ ፣ በአትክልትና በፍራፍሬ የተሰማሩ ከ120 በላይ የአገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል የአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ኩባንያዎች ይገኙበታል ተብሏል።

የዘንድሮው ዓውደ ርዕይ ለሰባተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ፕሮዲዩሰር ኤክስፖርተርስ አሶሴዬሽን ገልጿል፡፡

የአሶሲዬሽኑ የኮሙኒኬሸን አስተባባሪ አቶ አያሌው መኮንን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት የአወደርእዩ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን ሆልቲካልቸር ሴክተር ለማስተዋወቅ፣ የሃገር ውስጥና የውጭ ባለኃብቶችን ለመሳብና አምራቾችን ከግብዓት አቅራቢዎች ለማስተዋወቅ ነው፡፡

በአውደርእዩ ላይ በአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣  አፍሪካ እና አውስትራሊያ የሚገኙ  አምራቾች፣ አቅራቢዎች፣ አማካሪዎች፣ የሎጅስቲክ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ገዢዎች፣ የንግድ አማካሪዎችና የችግኝ አቅራቢዎች ይሳተፋሉ።  

ከአውደ-ርዕዩ ጎን ለጎን ዘርፉን በሚመለከቱ በተቋማት ማህበራዊ ኃላፊነትና የፋይናንስ ምንጮች ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

የመስክ ጉብኝት እንደሚካሄድም ነው የገለጹት አስተባባሪው፡፡

ኢትዮጵያ ለሆርቲካልቸር ምርት አመቺ ከሚባሉ ሃገራት አንዷ ናት፤ ይሁንና ብዙ ቢሊዮን ዶላር ማመንጨትና የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችለው የግብርና ኢኮኖሚ ዘርፍ ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር ከአቅም በታች መሆኑን ከአሴስሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢትዮጵያ ከአበባ የውጭ ገበያ ባለፈው ዓመት ያገኘችው 228 ሚሊዮን ዶላር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም