ቀጥታ፡

የተለያዩ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ሀዘናቸውን እየገለፁ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011 በኢትዮጵያ መቀመጫቸውን ያደረጉ የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ሳቢያ ህይወታቸውን ላጡ ሀዘናቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።

ኤምባሲዎቹ ሀዘኑን በማስመልከት በዛሬው እለት ሰንደቅ ዓላማቸውን ዝቅ አድርገዋል።

የኖርዌይ፣ የዴንማርክ፣ የእንግሊዝ፣ የካናዳና አሜሪካ ኤምባሲዎች በደረሰው አደጋ ማዘናቸውን ከገለፁት መካከል ናቸው።

በመግለጫቸውም ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዲንት ባራክ ኦባማ እና ባለቤታቸው ሚሸል ኦባማ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጀት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢ.ሲ.ኤ) የደረሰውን አደጋ በማስመልከት በአዲስ አበባ ቢሮው ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጓል። 

የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 የሆነው ይህ አውሮፕላን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር ጉዞ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃ በኋላ ነበር የተከሰከሰው።

በኢትዮጵያ ምድር ቢሾፍቱ ትላንት በደረሰው በዚሁ የአውሮፕላን የመከስከስ አደጋ የ35 አገራት ዜግነት ያላቸው መንገደኞች ህይወት አልፏል።

አደጋው ከደረሰ በኋላ እስካሁን የኢትዮጵያና የቻይና አየር መንገዶች ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ሞዴል ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይበር አግደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም