ቀጥታ፡

የዓድዋ ነዋሪዎች ለሕዳሴው ግድብ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸው ተጠቆመ

አክሱም ግንቦት 22/2010 የዓድዋ ከተማ ነዋሪዎች ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ 3 ሚሊዮን 100 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ። የከተማው ህዝብ ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ነው። የዓድው ከተማ ህዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጻድቃን ገብረማርያም ለኢዜአ እንዳሉት፣ የከተማው ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ዘንድሮ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገባው 5 ሚሊዮን ብር ውስጥ 3 ሚሊዮን 100 ሺህ ብር ያህሉን ማሰባሰብ ተችሏል። ከከተማው በዘጠኝ ወራት ውስጥ ገቢ የተደረገው ገንዘብ የተገኘው የመንግስት ሠራተኞች፣ የከተማው ነዋሪዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብና የግል ባለሀብቶች ባደረጉት መዋጮ ነው። በከተማው በቦንድ ግዢ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 3 ሚሊዮን ብሩን በማዋጣት የጎላ ድርሻ የነበራቸው የአደዋ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤትና የአድዋ አጠቃላይ ሆስፒታል ናቸው። የከተማው የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፣ የግድቡን ግንባታ ሥራ ለማፋጠን የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች በየዓመቱ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል። ዘንድሮም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች የሁለት ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን አቶ ካሳሁን ተናግረዋል። ከሦስት ዓመት በፊት የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች በተመሳሳይ መልኩ የአንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስም ድጋፉቸውን እንደሚቀጥሉ ኃላፊው አረጋግጠዋል። በአድዋ ከተማ የመንግስት ሰራተኛ የሆነው ወጣት ጽጌ ተክለማርያም በበኩሉ " ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የማደርገው አገራዊ ግዴታዬን በመወጣት በግድቡ የራሴን አሻራ ለማኖር ነው" ብሏል። ለግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን ሰባተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግም በቅርቡ የአንድ ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጉን አመልክቷል። በለግድቡ ግንባታ በየዓመቱ የአንድ ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት የጀመረውን ድጋፍ እንደሚቀጥልበት ነው ወጣቱ የገለጸው። በከተማው የባጃጅ ሹፌር ወጣት ብርሃነ አታክልቲ በበኩሉ ቀደም ሲል በአቅም ማነስ ምክንያት በሞራልና በሀሳብ በስተቀር የገንዘብ ድጋፍ ሳያደርግ መቆየቱን ተናግሯል። "በተያዘው ዓመት የራሴን ሥራ ስለጀመርኩ በየወሩ ሁለት መቶ ብር ገንዘብ በመቆጠብና ቦንድ በመግዛት ለግደቡ ግንባታ የበኩሌን ድጋፍ ለማድረግ አቅጄ እየሰራሁ ነው" ብሏል። በአድዋ ከተማ በቴራዞና ሴራሚክስ ማምረት ሥራ እንደተሰማራ የገለጸው ወጣት ቴዎድሮስ፤  የማህበሩ አባላት ሰርተው ከሚያገኙት ገቢ ለግደቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ለማድረግ በጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም