አየር መንገዱ በአደጋው ማዘኑንና ለተጎጂ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ በአደጋው ማዘኑንና ለተጎጂ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ
አዲስ አበባ መጋቢት 1/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፕላን መከስከስ አደጋው ማዘኑንና ለተጎጂ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ።
አደጋውን አስመልክቶ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራሩት አውሮፕላኑ ከጠዋት 2 ሰዓት ከ38 ደቂቃ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ቢነሳም ከስድስት ደቂቃ በኋላ ከራዳር ውጪ ሆኗል።
አውሮፕላኑ 149 ተሳፋሪዎችንና ስምንት የበረራ ሰራተኞችን ይዞ ሲጓዝ በነበረበት ወቅት በቢሾፍቱና ሞጆ መካከል በምትገኘው ኤጄሪ አካባቢ መከስከሱን ነው ያስረዱት።
አየር መንገዱ ቦይንግ 737 የተሰኘውን ይህን አውሮፕላን ከአራት ወራት በፊት መረከቡን ገልፀው ከአውሮፕላኑ አዲስነት በተጨማሪ በበረራው የተሳተፉት አብራሪውና ረዳቱ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ባለፈው ወር ምርመራ እንደተደረገለትና ከደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከበረራ የተመለሰ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከጆሃንስበርግ መልስ ለሶስት ሰዓታት እረፍት ማድረጉንና በዚህም ወቅት የቴክኒክ ምርመራ ተደርጎለት እንደነበርም ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።
ይሁንና የአውሮፕላኑ አብራሪው ችግር ገጥሞት እንደነበር ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አሳውቆ እንደነበር ነው አቶ ተወልደ የተናገሩት።
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተወልደ በአደጋው 32 ኬኒያውያን፣ 18 ካናዳዊያን፣ 17 ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም የሌሎች አገራት ዜጎች ተሳፍረው እንደነበር ነው የገለፁት ።
አየር መንገዱ ለሟች ቤተሰቦች የሚችለውን እንደሚያደርግ የተናገሩት አቶ ተወልደ ለመንገደኞችና ለሰራተኞቹ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶች መፅናናትን ተመኝተዋል።