ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ 157 ሰዎች በሞቱበት የአውሮፕላን አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ

አዲስ አበባ መጋቢት 1/2011 ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ 157 ሰዎች ህይወታቸውን ባጡበት የአውሮፕላን አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ።

ፕሬዝዳንቷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ እያለ አደጋ አጋጥሞት የመከስከሱን ዜና በከፍተኛ ድንጋጤና መሪር ሀዘን እንደሰሙ ገልጸዋል።

"ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ትልቅ የሀዘን ቀን ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቷ "በዜጎቻችንና ሌሎች የአየር መንገዱ ደንበኛ መንገደኞች ላይ በደረሰው አደጋ ልቤ ተሰብሯል" ብለዋል።

በአደጋው ተጎጂ ለሆኑ ቤተሰቦች ፣ ወዳጅ ዘመዶችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።

በተመሳሳይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላን አደጋ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጾ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡ መፅናናትን ተመኝቷል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)ም እንዲሁ በአደጋው የተሰማውን ሀዘን በመግለጽ የሟች ወገኖች ነፍስ በአፀደ ገነት እንዲያርፍ ፣ ለወዳጅ ዘመድ ቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መፅናናትን ተመኝቷል።

ዛሬ ማለዳ 149 መንገደኞችን እና ስምንት የበረራ ሰራተኞችን ይዞ ሲጓዝ የነበረው ቦይንግ 737 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ኬንያ ናይሮቢ በመብረር ለይ እየለ ባጋጠመ ችግር በምሥራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ ተከስክሶ የሁሉም መንገደኞች ህይወት አልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም