ኅብረተሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማዘውተር ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራሱን እንዲጠብቅ ተጠየቀ

91

ጋምቤላ መጋቢት 1/2011 በጋምቤላ ኅብረተሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማዘውተር ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራሱን እንዲጠብቅ ተጠየቀ።

"ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ለጤናማ ሕይወት!" በሚል መሪ ቃል የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የአመራር አካላት የተሳተፉበት የሁለት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ዛሬ በከተማው ተካሂዷል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተንኳይ ጆክ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳመለከቱት ኅብረተሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማዘውተር ከበሽታዎቹ ሊጠብቅ ያስፈልጋል፡፡

ለክልሉ ብሎም ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ መሠረቱ ብቁና ጤናውን የጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር እያንዳንዱ ዜጋ እንቅስቃሴውን ማዘውተር አለበት ብለዋል፡፡

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፖል ቤል በበኩላቸው የክልሉን ሕዝብ  ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመጠበቅ ቢሮው የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን እያከናወነ ነው።በየወሩ መጨረሻም የእግር ጉዞ መርሃ ግብር እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡

በተለይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር ከሚከላከላቸው በሽታዎች መካከል የደም ግፊትና የስኳር በሽዎች ይገኙበታል። ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደትንም ለመቆጣጠር ያስችላል።

በቀጣይም በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች ተመሳሳይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማስፋፋትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች  እንደሚጠናከሩ አስታውቀዋል፡፡

የእግር ጉዞው ተሳታፊዎች የደም ግፊትና የስኳር በሽታዎች ምርመራ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም