ቀጥታ፡

አየር መንገዱ በአውሮፕላን አደጋ በደረሰው ሕይወት መጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገለጸ

አዲስ አበባ  መጋቢት 1/2011 ዛሬ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ቦይንግ 737 በደረሰው አደጋ የሰው ሕይወት በመጥፋቱ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን አየር መንገዱ ገለጸ።

አውሮፕላኑ ምንም ዓይነት ቴክኒካዊ ችግር እንዳልነበረበትም አመልክቷል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በሰጡት መግለጫ፤ በአውሮፕላኑ መከስከስ የመንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ሕይወት በማለፉ ከፍተኛ ሃዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በአደጋው 149 ተሳፋሪዎችና ስምንት የበረራ ባለሙያዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ህይወታቸው ያለፉት ቤተሰቦችና ወገኖች ማስተናገጃ በአዲስ አበባ እና በናይሮቢ ቢሮ መከፈቱን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ 1ሺ 200 ሰዓታትን የበረራ ሰዓት ያስመዘገበው አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ለበረራ የተነሳው 2 ሰዓት ከ38 ደቂቃ ሲሆን፤ 2 ሰዓት ከ40 ላይ ችግር እንዳጋጠመውና ከራዳር እይታ ውጪ እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ከተረከበው አራት ወር የሆነው ቦይንግ 737 ወደ ኬንያ የሚያደርገወን ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ከጆሃንስበርግ ደቡብ አፍሪካ ተመልሶ ለሶስት ሰዓት ያህል አርፏል።

ይሄው በዋና አብራሪ ካፒቴን ያሬድ ሙሉጌታ ወደ ኬንያ እየተጓዘ የነበረው አውሮፕላን፤ ቀደም ብሎ በተካሄደ የቴክኒክ ፍተሻ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልነበረበት አመልክተዋል።

ረዳት አብራሪው አህመድ ኑር መሃመድ ኑር የሚባል ሲሆን፤ ከ200 ሰዓታት በላይ መብረሩም ተገልጿል።

የአደጋው መንሰኤ አለማቀፍ የአቬሽን ሕግን በተከተለ መልኩ ዓለምአቀፍ ምርመራ ተካሂዶ ዝርዝር መረጃው ወደፊት እንደሚገለጽ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም