በኢሉአባቦር ዞን በበልግና መኸር ከ132 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል

63

መቱ መጋቢት 1/2011 በኢሉአባቦር ዞን በበልግና መኸር አዝመራ ወቅቶች ከ132 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ የዞኑ ቡና፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጌታሁን ለገሠ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ዝግጅቱ እየተካሄደ ያለው በዞኑ 13 የገጠር ወረዳዎች ነው።

በአጠቃላይ ከሚለማው መሬት ውስጥ 22 ሺ 400 ሄክታር የሚሆነው በሙሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ለመሸፈን መታቀዱን አስታውቀዋል።

ለአርሶ አደሮቹ ከ65 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለማሰራጨት የታቀደ ሲሆን፤ እስካሁንም 30 ሺህ 800 ኩንታል የሚሆነው ተሰራጭቷል።

በዞኑ 70 በመቶ የሚሆነው ማሳ በመህር ቀሪው ደግሞ በበልግ ወቅት እንደሚለማ ኃላፊው አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው የበልግ እርሻ እንቅስቃሴም ከ15 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ታርሶና ለስልሶ ለዘር መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

በወቅቶቹ ለሚለማው ሰብል በግብዓት አጠቃቀም፣ በማሳ ዝግጅትና በሌሎችም ዘዴዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና ለግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመቱ ወረዳ የቡሩሳ ቀበሌ አርሶ አደር ጉታ ፊሪሳ በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ ለእርሻ ሥራ አመቺ በመሆኑ ማሳቸውን ለልማቱ እያዘጋጁ ነው።

አርሶ አደሩ እንደሚሉት ሁለት ሄክታር ማሳቸውን በበቆሎ፣ማሽላና ጤፍ የሚያለሙ ሲሆን፣ ካለፉት ዓመታት የተሻለ ምርት ለማግኘት ግብዓት ለመጠቀም እየተንቀሳቀሱ ናቸው።

በኢሉአባቦር ዞን በሁለቱ ወቅቶች ከሚለማው እርሻ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።

ይህም ከዓምናው በ100 ሺህ ኩንታል ምርት ብልጫ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም