የቡና የግብይት ማዕከል መቱ ከተማ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የቡና የግብይት ማዕከል መቱ ከተማ ተከፈተ
መቱ የካቲት30/2011 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አገልግሎቱን በቅርበት ለማቀላጠፍ ተጨማሪ የቡና የግብይት ማዕከል በኢሉአባቦር ዞን መቱ ከተማ ከፈተ፡፡
የግብይት ማዕከሉ በመቱ ከተማ መክፈቱ ከተጨማሪ ወጪና እንግልት እንደታደጋቸው ተገልጋዮች ገልጸዋል፡፡
በምርት ገበያው የመቱ ግብይት ማዕከል የደምበኞች አገልግሎት ተቆጣጣሪ አቶ አብዱልሀይም ኑሪ እንደገለጹት ቅርንጫፉ ካለፈው ሳምንት አንስቶ በኢሉአባቦር ዞን ለሚገኙ ቡና አቅራቢዎች አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
የቅርንጫፉ በመቱ ከተማ መከፈት የቡና ነጋዴዎች ከዚህ ቀደም ለግብይት እስከ በደሌ 120 ኪሎ ሜትር ድረስ በመጓዝ የሚያጠፉትን ግዜና ወጪ በመቀነስ አገልግሎቱን በቅርበት ለማቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
"ህገወጥ የቡና ንግድን በመከላከል ነጋዴዎችና አርሶ አደሮች ብዛት ያለው የቡና ምርት በማዕከሉ በኩል እንዲገበያዩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል" ብለዋል።
ቅርንጫፉ የግብይት አገልግሎቱን የሚሰጠው በቡናው ዘርፍ መሆኑን ገልጸው በዚህም ከዞኑ 14 ወረዳዎች የሚገኙ ነጋዴዎችና አርሶ አደሮች በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡
ግብይቱ ከተጀመረ ከአንድ ሳምንት ባይበልጥም በአሁኑ ወቅት እስከ 90 የጭነት ተሽከርካሪዎች የቡና ምርት በየዕለቱ እየገባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቅርንጫፉ የናሙና ተቆጣጣሪ አቶ ኢዶሳ አምቢሳ በበኩላቸው "ከዚህ ቀደም ነጋዴዎች ቡና ጭነው ረጅም ርቀት ሲጓዙ ከሌሎች ሰብሎች ጭምር ስለሚጭኑ የጥራት መጓደል ችግር ያጋጥም ነበር " ብለዋል፡፡
የግብይት ማዕከሉ የቡና ምርት ባለበት አካባቢ መከፈቱ ይህን ችግር ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በግብይት ማዕከሉ ሲገለገሉ ከነበሩት መካከል አቶ ግዛው ግርማ በሰጡት አስተያየት የግብይት ማዕከሉ በአቅራቢያቸው መከፈቱ ለመኪና ኪራይ ሲያወጡ የነበረውን ወጪ ከመቀነሱ ባለፈ ምርታቸውን በቅርበት ያለ ወኪል ለመከታተል እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡
የቡና ምርት ሳያከማች በፍጥነት ለገበያ እንዲቀርብና ጥራቱ እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡
የኢሉአባቦር ዞን ቡና፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ለገሰ በበኩላቸው የግብይት ማዕከሉ በመቱ ከተማ እንዲከፈት የባለድርሻ አካላት የረጅም ግዜ ጥያቄ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የግብይት ማዕከሉ በከተማው መከፈት አርሶ አደሩ በቡና ልማትና ጥራት አጠባበቅ ያለውን ተነሳሽነት እንደሚያሳድገው ጠቅሰው "የተሻለ የሚያመርቱ አርሶአደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለምርት ገበያ ለማቅረብ ይበልጥ እንዲሰሩ ያነሳሳል" ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቡና አምራች የሆኑ ዘጠኝ አርሶ አደሮች በቀጥታ ምርታቸውን በምርት ገበያ በኩል ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ጌታሁን በቀጣይም የአርሶ አደሮቹን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በኢሉአባቦር ዞን በየዓመቱ ከ60 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ቢሰበሰብም ለገበያ የሚቀርበው ግን ከ35 ሺህ ቶን እንደማይበልጥ ተመልክቷል፡፡