ለ4ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ዝግጅት ተጠናቋል....የፌዴራል ስታስቲክስ ኤጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
ለ4ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ዝግጅት ተጠናቋል....የፌዴራል ስታስቲክስ ኤጀንሲ
ባህር ዳር የካቲት 30/2011 በመላ ሀገሪቱ በመጋቢት ወር መጨረሻ ለሚካሄደው 4ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የፌዴራል ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።
“ጥራት ያለው የመረጃ አያያዝ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር 28ኛው ዓመታዊ ጉባኤ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት እንደሀገር አራተኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ በጥራት ለማካሄድ ሲደረግ የቆየው ዝግጅት ተጠናቆ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
በህዝብና ቤት ቆጠራው የሚሳተፉ 180 ሺህ ቆጣሪዎችና ተቆጣጣሪዎች፣ እንዲሁም አምስት ሺህ የሚደርሱ አስተባባሪዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ውጤታማ ቆጠራ ለማካሄድም ኤጀንሲው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በተቋም አቅም ግንባታ፣ በአሰራር ዝግጅት፣ ለቆጠራው የሚሆን የሰው ኃይል የማዘጋጀትና መሰል ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
በተጨማሪም ተቋሙ ራሱን የማጠናከር፣ የተሳኩ ቆጠራ ያደረጉ ሀገሮችን ልምድና ተሞክሮ የመቅሰም፣ የተሻለ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን በማስመጣት ለባለሙያዎች ስልጠና የመስጠት ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።
ውጤታማ ሥራ ለመስራት ኤጀንሲው ቆጠራውን በሁለት መንገድ ለማካሄድ መዘጋጀቱን የገለጹት አቶ ቢራቱ "አንደኛው ሰው በተገኘበት ቦታ መቁጠር ሲሆን ሁለተኛው ሰውን በመደበኛ መኖሪያ ቦታው የመቁጠር ስራ ይከናወናል" ብለዋል።
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስና ኢኮኖሚክስ ማህበራት፣ ከስነህዝብና፣ ከዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎችን በ40 ቡድን በማደራጀት በታዛቢነት እንዲሰሩ የሚደረግ አመሆኑ አመልክተዋል።
"ታዛቢዎቹም በመስክ የሚካሄዱ ቆጠራዎችን አካሄድ፣ ቆጠራው ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ማሟላቱንና ቆጠራው በትክክል መካሄዱን በመታዘብ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይደረጋል" ብለዋል።
መንግስት ሁሉንም የልማት ዕቅዶች የሚያከናውነው ከእያንዳንዱ ዜጋ በሚሰበሰበው መረጃ ተመስርቶ በመሆኑ ህዝቡ ይህን በመገንዘብ በቆጠራ ወቅት ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጥ አሳስበዋል።
ለቆጠራው የሚያገለግሉ 180 ሺህ ታብሌቶች፣ 126 ሺህ የኃይል ማከማቻ ፓወር ባንኮችና 35 ሺህ ሶላር ቻርጀሮች መዘጋጀታቸውን አቶ ቢራቱ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር መርጋ በሊና በበኩላቸው ማህበሩ 4ኛ ዙር የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የመረጃ ጥራቱ እንዲጠበቅ የሙያ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ማህበሩ 28ኛ ዓመታዊ ጉባኤውን እያካሄደ ያለውም በመረጃ አሰባሰብና አያያዝ ጥራትና በ4ኛው ዙር የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።
"የቆጠራው ውጤት ለሀገሪቱ ቀጣይ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ ማህበሩ ስለቆጠራው ጠቀሜታ ለህዝቡ ትኩረት ሰጥቶ የማስገንዘብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል" ብለዋል።
ማህበሩ የኤጀንሲው አማካሪ ቦርድ አባል በመሆኑ ሂደቱን ከቆጠራው በፊት፣ በቆጠራው ወቅትና ከቆጠራ በኋላ ምን እንደሚመስልና መረጃው ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲሰበሰብ ከ500 በላይ አባላቱን በታዛቢነት እንደሚያሰማራም አስረድተዋል።
የማህበሩ አባልና በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ፀጋ ካሳየ በበኩላቸው ቆጠራው በስኬት እንዲጠናቀቅ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለቆጠራው ፋይዳ ለሕብረተሱ እያሳወቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።