የዓመታት የቦታ ጥያቄያቸው ምላሽ በማገኘቱ መደሰታቸውን የአላማጣና ማይጨው ከተማ ወጣቶች ገለጹ

57

ማይጨው  የካቲት 30/2011 ለዓመታት ሲያቀርቡት የነበረው የቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን በትግራይ ደቡባዊ ዞን አላማጣና ማይጨው ከተማ የሚኖሩ አንዳንድ ወጣቶች ገለጹ።    

የትግራይ ደቡባዊ ዞን ንግድና ከተማ ልማት መምሪያ በበኩሉ ከቤተሰብ ጋር በጥገኝነት ይኖሩ ለነበሩ ወጣቶች ለመኖሪያ ቤት መስሪያ እንዲውል ከ600 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት መስጠቱን አስታውቋል።

የአላማጣ ከተማ ነዋሪ ወጣት ተስፋይ ካህሳይ እንዳለው በገጠር ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚኖሩበት ቤት ወደ ከተማ ሲካለል መሬት አልባ ሆነው እንደነበር ተናግሯል፡፡

" በአሁኑ ወቅት መንግስት የወጣቱን ችግር ተገንዝቦ በወላጆቻችን እጅ የነበረ የመንግስት ትርፍ ቦታ ለመኖሪያ ቤት መስሪያ በመፍቀዱ ተደስቺያለሁ" ብሏል።

የቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ በመቆየቱ ቅሬታ አድሮበት እንደነበር የገለጸው ደግሞ ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወጣትሃፍቱ አያሌው ነው፡፡

" ከሰባት ዓመታት በኋላ መንግስት ዘግይቶም ቢሆን ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ በመስጠቱ ደስተኛ ነኝ " ሲል ተናግሯል።

የገጠር አካባቢዎች ወደ ከተማ ሲካለሉ በቤተሰብ ስር የነበረውወጣት እጣ ፈንታ መዘንጋት እንደሌለበት የገለጸው ደግሞ የማይጨው ከተማ ነዋሪ ወጣት ካህሳይ ግርማይ ነው።

"ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ መንግስት በየጊዜው ስናነሳው ለነበረው ጥያቄ እልባት በመስጠቱ ቅሬታችን ተወግዷል" ብሏል።

የትግራይ ደቡባዊ ዞን ንግድና ከተማ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስመላሽ ረዳ በበኩላቸው ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ ስምንት ከተሞች ለመኖሪያ ቤት መስሪያ የተዘጋጀ ቦታ ለ4 ሺህ 340 ወጣቶች መታደሉን ተናግረዋል።

የወጣቶቹ የመሬት ጥያቄ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲነሳ መቆየቱን ያስታወሱት ኃላፊው፣ በጊዜው ፈጣን ምላሽ አለመሰጠቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።

የመሬት እደላው በተለይ ላለፉት አራት ዓመታት በዋናነት ሲንከባለል የቆየው ግልጽ የሆነ የማስፈጸሚያ መመሪያ ባለመኖሩ ጭምር መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል።

የክልሉ መንግስት ችግሩን አጢኖ በቀበሌዎችና ከተሞች ርክክብ ወቅት ቦታ ሳይሰጣቸው የተዘነጉ ወጣቶቹ የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ተግባራዊ መደረጉን አቶ አስመላሽ አመልክተዋል፡፡

እንደእርሳቸው ገለጻ  አብዛኞቹ ወጣቶች በከተሞቹ ውስጥ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል 140 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ በነፍስ ወከፍ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የተወሱኑት ወጣቶች በወላጆቻቸው ሥር የነበረ የመንግስት ትርፍ ቦታ ህጋዊ መንገድን በተከተለ ሁኔታ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።

ለወጣቶች የቦታ እደላ ሲባል ከመሬታቸው ለተነሱ ገበሬዎች ከ 76 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መፈጸሙን  መረጃዎች  ያመላክታሉ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም