አየር መንገዱ የአቪዬሽን ሙያተኞች በአውሮፓ አገሮች ስራ እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ የአቪዬሽን ሙያተኞች በአውሮፓ አገሮች ስራ እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 30/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገሪቱም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ያለውን የስራ አጥ ችግር ለመፍታት በአቪዬሽን ዘርፍ ሙያተኞችን ከማሰልጠን ባሻገር በአውሮፓ አገሮች ስራ እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
የአየር መንገዱ አቪዬሽን አካዳሚ በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 559 ሙያተኞች ዛሬ አስመርቋል።
በአካዳሚው ለሦስት ዓመት በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በአውሮፕላን ጥገና፣ በበረራ አስተናጋጅነት፣ በግብይት እንዲሁም በሌሎች የደንበኞች አገልግሎት መስኮች የሰለጠኑ ናቸው።
ከተመራቂዎቹ ውስጥ40 በአውሮፕላን አብራሪነት፣ 58 በአቪዬሽን ጥገና እና 123 በበረራ አስተናጋጅነት፣ 286 በግብይት ዘርፍ እንዲሁም 52 ደግሞ በምግብ እና በሌሎች የደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ የሰለጠኑ ናቸው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ በአቪዬሽን ዘርፍ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በአውሮፓ አገሮች ስራ እንዲያገኙ አየር መንገዱ ጥረት እያደረገ ነው።
የአቪዬሽን ዘርፍ በጣም ፈተናዎች የሚበዙበት የሙያ ዘርፍ መሆኑን ገልጸው ሙያተኞች በፍጹም ስነ-ምግባርና ትህትና በተሞላ መንፈስ ማገልገል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
አካዳሚው አሁን ከሚሰጣቸው የስልጠና መስኮች በተጨማሪ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በአመራርነት እንዲሁም በምግብ ዝግጅትና አቅርቦት ስልጠና ለመስጠት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደበበ በበኩላቸው የአቪዬሽን አካዳሚው በአሁኑ ወቅት በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በመምራት ላይ ይገኛል።
በዚህም አካዳሚው የሰለጠኑና በሙያቸውና በስነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ ባለሙያዎችን ከአገር ውስጥ አልፎ ለአለም አለቀፍ ደረጃ ለማፍራት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ተመራቂዎቹ በሰለጠኑበት የሙያ መስክ አገራቸውንና ህዝባቸውን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል ቃል ገብተዋል።
አካዳሚው በአሁኑ ወቅት በዓመት ከ1 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያሰለጥን ሲሆን የቅበላ አቅሙን እ.አ.አ በ2030 ወደ 4 ሺህ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ አለው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን አካዳሚ ከተመሰረተ 60 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ከምስረታው አንስቶ እስከ አሁን ድረስ 16 ሺህ 100 ሰዎችን አሰልጥኖ አስመርቋል። ከዚህ ውስጥ ከ48 የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለመጡ 2 ሺህ ሰዎች ስልጠና ሰጥቷል።