ቀጥታ፡

የስልክ ኔትወርክ እንዳይቋረጥ የሚያደርጉት ባትሪዎች በኤሌክትሪክ መቆራረጥ የተነሳ ሃይል የመቆጠብ አቅማቸው ተዳክሟል

አዲስ አበባ  የካቲት 30/2011 በኢትዮ ቴሌኮም ኔትወርክ እንዳይቋረጥ የሚያገለግሉት ኃይል ቆጣቢ ባትሪዎች በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የተነሳ ከጥቅም ውጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ኢትዮ-ቴሌኮም አስታወቀ።

በተቋሙ የኔትወርክ ዲቪዥን ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ኃይለመስቀል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ከስልክ ኔትወርክ መቆራረጥና መጥፋት እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት ጥራት ጋር በተያያዙ የሚታዩ ችግሮች"  አስመልከቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት የሚታየው የኔትወርክ መጥፋት ዋነኛ ምክንያት የኤሌክትሪክ መቆራረጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም እንደ ሁለተኛ የሃይል አማራጭ የሚያገለግሉት አብዛኛዎቹ ጀነሬተሮች በውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ መለዋወጫ ስላልተገዛላቸው አገልግሎት በማቆማቸው ለኔትወርክ መቆራረጡ ሌላ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስራ አስኪያጁ "በተለይ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ህብረተሰቡ እያገኘ ያለው የስልክ አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱንና አንዳንድ ቦታ ላይ የመቋረጥ ሁኔታ እየታየ መሆኑን እኛም የገመገምነውና ችግሩ መኖሩን የምናምንበት ነው" ሲሉ መልሰዋል።

ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ጋር ተያይዞ በቀን በርካታ የኔትወርክ ጣቢያዎች ስራ ማቋረጣቸው ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ 730 የሞባይል ኔትወርክ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን መብራት ሲጠፋ ሃይል በመቆጠብ ኔትወርክ እንዳይቋረጥ የሚያደርጉ ባትሪዎች ቢገጠሙም ኤሌክትሪክ ቶሎ ቶሎ ስለሚቋረጥ የቻርጅ አቅማቸው እያነሰ ከጥቅም ውጭ እስከመሆን ደርሰዋል።

በአንድ ጊዜ የሰበሰቡትን ሃይል እስከ አራት ሰአት የማቆየት አቅም የነበራቸው ባትሪዎች አሁን የሚያገለግሉት ለአስር ደቂቃና ከዛ በታች  መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ 7 ሺ 200 የኔትወርክ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን በብዙዎቹ ጣቢያዎች የሚገኙ ባትሪዎች መድከማቸውን ነው ስራ አስኪያጁ የተናገሩት።

"ባትሪዎቹ መድከማቸው እየታወቀ ለምን ለመግዛት አልታሰበም፣ የጀነሬተር መለዋወጫስ እንዴት አይኖርም" ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ባትሪዎቹን ለመተካት ከሶስት አመት በፊት ኮንትራት ቢፈረምም በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ሳይሳካ መቆየቱን ተናግረዋል።

''ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሬው ተገኝቶ ባትሪዎቹን ለመግዛት ከአስመጭዎች ጋር በአዲስ መልክ ኮንትራት ተፈራርመን ወደ ስራ ልንገባ ነው'' ብለዋል።

"ይህ ተግባራዊ እስከሚሆን ለህዝቡ ምን አማራጭ አቅርባችኋል" ለሚለው ጥያቄም ባትሪዎችን ከአንዱ ጣቢያ ወደ ሌላ ጣቢያ የማተካካት ስራ እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል።

የጀነሬተሮቹን መለዋወጫ በተመለከተ እስካሁን የዘገዩት በውጭ ምንዛሬ እጥረት መሆኑንና በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ መለዋወጫ ተገዝቶላቸው ጥገና ላይ መሆናቸውንና በቅርቡ በርካታ ጀነሬተሮች ወደ ስራ እንደሚገቡም ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር የአስቸኳይ ምላሽ ስምምነት ለማድረግ በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ስምምነቱ የቴሌ ጣቢያዎች አካባቢ የኤሌክትሪክ ችግር እንዳያጋጥምና ሲያጋጥምም ልዩ የሰው ሃይል ተመድቦለት በፍጥነት የሚፈታበት አሰራር እንዲኖር ሲሆን ለዚህም ቴሌ የተለየ ክፍያ እንደሚፈጽም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም