ወጣቱ ትውልድ ለሰላምና ለሀገራዊ ለውጡ ስኬት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ

84

ድሬዳዋ የካቲት 30/2011 ወጣቱ ትውልድ ለሀገሩቱ ሰላምና ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ ስኬታማነት ኃላፊነቱን በትጋት ሊወጣ እንደሚገባ የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡

ለሉሱ (ድንቅነሽ) ትናንት በድሬዳዋ በተደረገው የአቀባበል ስነስርአት ላይ የተገኙት የኢፌድሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ እንዳሉት፣ ዜጎች በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣና ሀገራዊ ለውጡ እንዲጠናከር የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።

በተለይ ወጣቱ ትውልድ በመደመር መንፈስ ለሀገር ሰላምና ሁለንተናዊ ዕድገት መረጋገጥ ሌት ተቀን እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሉሲ ጉዞ ዋነኛ ዓላማ የሰላም አምባሳደር በመሆን የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ሁሉም ለሀገር ግንባታ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በድሬዳዋ ነዋሪዎች መካከል ለዘመናት የቆየውን በፍቅር፣ በሰላምና በጋራ የመኖር መገለጫ ይበልጥ ለማድመቅ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ነው አቶ ሀብታሙ የገለፁት፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው  አሁን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በውይይትና በመደማመጥ ከመፍታት ባለፈ በሀገሪቱ ያለውን የዕድገትና የለውጥ ጉዞ ለማሳካት ሁሉም መረባረብ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ከንቲባ ኢብራሂም እንዳሉት ወጣቱ ለዘላቂ ሰላም ትልቅ ዋጋ ከመስጠት ባለፈ የእናትና የአባቶችን ጽናት ተላብሶ የተሸለች ሀገር ለመገንባት ተግቶ ሊሰራ ይገባል፡፡

የሉሲ ወደ ድሬዳዋ መምጣት በሕብረተሰቡ መካከል የርስ በርስ ፍቅር፣ አንድነትና ሰላምን ይበልጥ ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥረም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

የጉዞ ሉሲ የሰላምና የፍቅር ልዑካን ቡድን አባላል የሆኑት የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በበኩላቸው አዲሱ ትውልድ የርስ በርስ ፍቅሩን በማጠናከር ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ሉሲ የሰላምና የፍቅር ጉዞን አስመልክቶ በነገው ዕለት የሰላም ሲምፖዚየም የሚካሄድ ሲሆን ሰኞ መጋቢት 1ቀን 2011ዓ.ም በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለሉሲ በተለያዩ ዝግጅቶች አቀባበል ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ጉዞ ሉሲ የሰላምና የፍቅር ጉዞ እስካሁን ድረስ በሰመራ፣ በጅግጅጋና በሐረር በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን በድሬዳዋም ሉሲ ለ5 ቀናት ቆይታ እንደሚኖራት ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም