በመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊነት የተሾሙት ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሃላፊነት ጉዞ - ኢዜአ አማርኛ
በመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊነት የተሾሙት ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሃላፊነት ጉዞ

አዲስ አበባ የካቲት 30/2011 በመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊነት የተሾሙት ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አገራቸውን ከማገልገል በተጨማሪ ወደ ዓለም አቀፍ ኃላፊነት መሸጋገራቸውን የሚያመላክት ነው።
በ1960 ዓ.ም የተወለዱት ዶክተር ወርቅነህ ከ1980ቹ መጀመሪያ አካባቢ የቀድሞው ኦህዴድ የአሁኑን ኦዴፓን በአባልነት የተቀላቀሉ ሲሆን ከፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባልነት እስከ ድርጅት ምክትል ሊቀመንበርነት መምራት ችለዋል።
የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስ እና በውጭ ግንኙነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ከሶስት ዓመታት በፊት ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በፖሊስ ሳይንስ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሰርተዋል።
ከ20 ዓመታት በላይ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገራቸውን ሲያገለግሉ የቆዩት ዶክተር ወርቅነህ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የትራንስፖርት ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በመሆን ሰርተዋል።
በ2009 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስም ኢትዮጵያ ከአገሮች ጋር ያላት ሰላምና ትብብር እንዲጠናከር፣ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስራዎች እንዲሁም ዜጎች አገራዊ አስተዋጿቸው እንዲጎለብት በማድረግ በርካታ ስራዎችን ማከናወን ችለዋል።
ላለፉት 20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት መቋጫ አግኝቶ የትብብር ግንኙነቱ ዳግም እንዲያንሰራራ በማድረግም ጉልህ ሚና ነበራቸው።
ከሌሎች አጎራባች አገሮች ማለትም ከሱዳን፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ጋርም በርካታ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲዎች ክንውን በእርሳቸው የኃላፊነት ዘመን ትኩረት ተሰጥቶት ተከናውኗል።
ከግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ሌሎች የቀጣናው አገራት ጋርም በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የዲፕሎማሲ ስራ በማከናወን ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።
ኢትዮጵያ በአሜሪካ፣ ሩስያ፣ ቻይናን ጨምሮ ሌሎች ኃያላን አገራት በዴፕሎማሲ መስክ ልዩ ትኩረት እንዲሰጣት በማድረግም ሚናቸው ከፍ ያለ ነበር።
በአፍሪካ ሕብረት፣ በኢጋድ፣ በአውሮፓ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባለብዙ ወገን ወዳጅነቷ እንዲጠናከር ማድረግም ችለዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ለመጣው ለውጥ የጎላ ሚና እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ዶክተር ወርቅነህ፤ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የዜጋ ዲፕሎማሲ በማከናወንም ስኬታማ እንደነበሩ ይጠቀሳል።
ዶክተር ዐብይ አህመድ አዲስ ካቢኔ ሲያዋቅሩ በነበሩበት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃላፊነት የቀጠሉት ዶክተር ወርቅነህ አሁን ላይ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ረዳት ዋና ፀሃፊ በመሆን ተሹመዋል።
በተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በድርጅቱ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ የተሾሙት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ባደረገችው አስተዋጽኦ እንዲሁም እርሳቸው ለድርጅቱ ዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት በተጫወቱት የመሪነት ሚና መሆኑም ታውቋል።
የሚኒስትሩ ሃላፊነት በናይሮቢ ኬንያ በድርጅቱ ስር የሚገኙ 18 ኤጀንሲዎችን የማስተባበር ኃላፊነት ሲሆን ሹመቱ ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን ላደረገችው አስተዋጽኦ የተሰጠ እውቅና መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የዶክተር ወርቅነህን መሾም ተከትሎም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት የእንኳን ደስ ያለዎት መልእክት አስተላልፏል።