ኤጀንሲው በስራ ላልነበሩ ሰራተኞች የደመወዝ ክፍያ የፈጸሙ ኃላፊዎችን በህግ እንዲጠይቅ ማሳሰቢያ ተሰጠው - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው በስራ ላልነበሩ ሰራተኞች የደመወዝ ክፍያ የፈጸሙ ኃላፊዎችን በህግ እንዲጠይቅ ማሳሰቢያ ተሰጠው
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በጡረታና በሞት ከስራ ለተገለሉ ሰራተኞች ደመወዝ የከፈሉ ሃላፊዎችን ለህግ እንዲያቀርብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሳበ። የምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የቀድሞውን የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ የ2008 በጀት አመት ሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ዛሬ አዳምጧል። ያለአግባብ የተከፈለ ደመወዝ፣ ገቢ በወቅቱ አለመሰብሰብ፣ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ስራ ላይ ያልዋለ በጀት፣ ለኦዲት ያልቀረበ የወጪ ማስረጃ፣ የተሽከርካሪ መኪኖች አያያዝና ንብረት አጠባበቅ ከሂሳብ ኦዲት ግኝቶች መካከል ናቸው። ኤጀንሲው በፌዴራል መንግስት ገንዘብ ክፍያ መመሪያ መሰረት ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ክፍያ አለመፈጸሙን የሂሳብ ኦዲት ግኝቱ አረጋግጧል። የሂሳብ ኦዲቱ እንደሚያሳየው አራት በጡረታ ለተገለሉ ሰራተኞችና አንድ በሞት ለተለዩ ሰራተኛ ከ66 ሺህ ብር በላይ እና ለሶስት ሰራተኞች ከ2ሺህ ብር በላይ ያልሰሩበት ደመወዝ ተከፍሏቸዋል። የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች የመንግስትን የፋይናንስ አሰራር ለምን እንደጣሱና በኦዲት አስተያየቱ መሰረት የተወሰዱ እርምጃዎችን እንዲያስረዱ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል። የኤጀንሲው የኮርፖሬት ሃብት ስራ አመራር ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አረጋይ ገብሬ፤ ክፍያው ጡረታ የሚወጡ ሰዎች ከደመወዝ መክፈያ ዝርዝር (ፔይ ሮል) እስኪሰረዙ ድረስ መፈጸሙን ገልጸው 'አሁን ገንዘቡ እንዲመለስ ተደርጓል' ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዲቢሶ ድርጊቱ በሌሎች መስሪያ ቤቶችም የሚስተዋል መሆኑን በመግለጽ 'ግለሰቦቹ ገንዘቡን ማስመለስ ብቻ ሳይሆን ከፋዮችና ተቀባዮች በህግ ተጠያቂ መሆን አለባቸው' ብለዋል። ሰራተኛውን ያሰራው የስራ ክፍል፤ የሰው ሃብትና ፋይናንስ ክፍሎች በሃላፊነታቸው መሰረትና ደመወዙን የወሰዱ ሰራተኞችን ኤጀንሲው ለህግ አቅርቦ የወሰደውን ማስተካከያ እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል። አንድ ግለሰብ ያልሰራበትን ደመወዝ መቀበል ወንጀል በመሆኑ ሰራተኛው የሰራበትን ብቻ እንዲወስድ በጥብቅ ያስገነዘቡት ዋና ኦዲተሩ 'ጉዳዩ ጥብቅ አሰራር ካልተበጀለት ትልቅ ችግር እየሆነ መጥቷል' ብለዋል። የቋሚ ኮሚቴው አባላት 'በህይወት ለሌለ ሰው እንዴት ደመወዝ እንደተከፈለ በማጣራት ድርጊቱን የፈጸሙት ኃላፊዎች ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት' ሲሉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። በሌላ በኩል የኤጀንሲው ንብረት የሆነ ቶዮታ ፓራዶ ተሽከርካሪ በኤጀንሲው አሽከርካሪ ስም ወጪ ሆኖ የቀድሞው ዋና ዳሬክተር በተቋሙ በነበሩበት ወቅት ሲጠቀሙበት እንደነበር ኦዲቱ ያመላክታል። ሆኖም 2008 ዓ.ም ወደ ሌላ መስሪያ ቤት ሲዘዋወሩ መኪናውን ይዘው መሄዳቸውና ኤጀንሲው ለማስመለስ ቢሞክርም 'ይዘው እንዲሄዱ የሚፈቅድ መመሪያ ወጥቷል' መባሉ በምክር ቤቱ አከራካሪ ጉዳይ ነበር። በተጨማሪም ኤጀንሲው በተለያየ ጊዜ ባዘጋጀው ስልጠና ሰልጣኞች የደመወዛቸውን መጠንና ከሚሰሩበት ተቋም አበል አለመውሰዳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ሳያመጡ ከ356ሺህ ብር በላይ መክፈሉ በኦዲት ቢረጋገጥም እስካሁን እርምጃ አልተወሰደም። የመንግስትን ገንዘብ ለብክነትና ለምዝበራ እንደሚዳርግ እየታወቀ የገበያ ጥናት ሳይደረግ ለተለያዩ እቃዎች ግዥና አገልግሎት ከ446 ሺህ ብር በላይ ተከፍሏል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት ገላሶ በሰጡት ማጠቃለያ የኤጀንሲው የግዥ አፈጻጸም ለብልሹ አሰራር የሚያጋልጥ በመሆኑ የመንግስትን ደንብና መመሪያ አክብሮ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል። በስራ ላይ ለሌሉ ሰራተኞች የተከፈለው ደመወዝ ኤጀንሲው እርምጃ ወስዶ በፍጥነት ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከተው አካል እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል። የቀድሞው ዋና ዳሬክተር ተቋሙን ሲለቁ ይጠቀሙበት የነበረውን መኪና ይዘው እንዲሄዱ የሚያዘውን አሰራርም ይፈተሻል ብለዋል። የቀድሞ የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ በ2008 ዓ ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣ ደንብ መሰረት የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ እንዲሁም የፌዴራል የመካከለኛና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ በሚል ወደ ሁለት ተቋምነት ተሸጋግሯል።