ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በየአመቱ ከመቶሺ ሰዎች በላይ በሳንባ በሽታ ይጠቃሉ … ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

የካቲት 29/2011 በኢትዮጵያ በሳንባ  በሽታ በየአመቱ ከመቶ ሺ ሰዎች በላይ እንደሚያዙ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የብሄራዊ ሳንባ በሽታ መከላከያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ታዬ ለታ እንዳሉት በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሳንባ በሽታ ስርጭት እየቀነሰ ቢመጣም  አሁንም በየአመቱ ከመቶሺ  ሰዎች በላይ በበሽታው ይያዛሉ ፡፡

ህክምናው በሀገሪቱ በሁሉም ሆስፒታሎች፣ጤና ጣቢያዎችና 60 ከመቶ ጤና ኬላዎችም ጭምር አገልግሎት ቢሰጥም የበሽታው ስርጭት አሁንም አሳሳቢነቱ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

በጤና ተቋማቱ አገልግሎቱን ለመስጠት የግብአት አቅርቦት ችግር ባይኖርም በሽታውን ለመርመር የላብራቶሪ ቴክኒሻን አጥረት መኖሩ ውጤታማነቱ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን አልሸሸጉም፡፡

በሀገራችን 80 ከመቶ የላብራቶሪ ባለሞያ እጥረት በመኖሩ ህሙማኑ የላብራቶሪን አገልግሎት ሌላ ቦታ በማሰራት በሚቀርባቸው ጤና ተቋማት አንደሚታከሙ ጠቁመዋል ፡፡

ህክምናውን ከጀመሩም 94 ከመቶዎቹ እንዲያጠናቅቁ ክትትል መደረጉን ያስረዱት አስተባባሪው   አልፎ አልፎ ህክምናቸውን ጀምረው ቦታ የሚቀይሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መድሀኒት ለተላመደ በሽታ መጋለጣቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም የበሽታው ስርጭት በከተሞች ሰዎች ተፋፍገው መኖራቸው በቂ ንጹህ አየር ዝውውር እንዳይኖር ማድረጉ፣ የተጨናነቀ ትራንስፖርት አጠቃቀም ለበሽታው ከፍተኛ ስርጭት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

ይህም ሀገራችንን በአለማችን መድሀኒቱን ከተላመደም ሆነ በሽታው ከተስፋፋባቸው 30 ሀገራት አንዷ እንድትሆን ማድረጉን በመግለጽ ችግሩንም ለመፍታት የተጠናከረ የግንዛቤና፣ አዳዲስ የህክምና መሳርያ በመገዛት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሰለሞን ጣፋ  መድሀኒት የተላመደ የሳንባ ነቀርሳ ታማሚ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለሳንባ በሽታ ህክምና የታዘዘለትን  መድሀኒትም ሆነ ህክምናውን በአግባቡ መከታተሉን ይናገራል፡፡ይሁን እንጂ በሽታው  ከሶስት አመታት በኋላ በማገርሸት ወደ መድሀኒት የተላመደ በሽታ በመለወጡ ለስምንት ወራት በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል እያታከመ መሆኑን ተናግሯል ፡፡  

ከሶስት አመት በፊት ለስድስት ወራት የሳንባ ህክምና አድርጋ ቢሻላትም አሁን ላይ በሽታው ወደ ሳንባ ነቀርሳ በመቀየሩ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ህክምና  መከታተሏን የምትነግረን ሜላት ያሲን ነች፡፡

ቀደም ሲል ለስድስት ወራት የሳንባ ህክምናውን በአግባቡ ቢጨርስም ከአንድ አመት በኋላ በሽታው መመለሱን የሚያስረዳው ወጣት  ዘላለም ብሩ  በሽታውም ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረጉንና የህክምና አሰጣጡም ጥሩ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ዶክተር አያሌው ትዛዙ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የደረትና የሳንባ ቀዶ ህክምና እስፔሻሊስትና የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የህክምና ቦርድ አባል እንዳሉት የብዙ ጊዜ ሳንባ ታማሚዎች  ወይም የአጣዳፊ የሳንባ  ቀዶ ህክምና ከሚደረግላቸው ህሙማን ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት መድሀኒቱን የተላመደ ሳንባ በሽታ ነው ፡፡

“ህክምናውን በተገቢው  በመውስድ በሽታው  ወደ ቀዶ ህክምና የመሄድ እድሉን መቀነስ ቢቻልም አልፎ አልፎ ከበሽታው አደገኛነት አለያም እንደማንኛውም በሽታ ጠባሳ ጥሎ በማለፉ የአተነፋፈስ ስርአት መዛባትና የሳምባ መድማት ያስከትላል” የሳንባ መጎዳት ቀጥታ ከደም ዝውውር ጋር በመገናኘቱም  ለዘርፈ ብዙ ጤና እክል ያጋልጣል ፡፡

እንደ ዶክተር አያሌው ገለጻ “በአክታ ናሙና የተገኘው የሳንባ በሽታ ህሙማኑ መድሀኒት መውስድ ጀምረውና ሁለትና ሶስት ወራት የመሻል ስሜት ከሌለው  ህክምናው ወደ ቀዶ ህክምና ለማምራት ማሳያ ሊሆን በመቻሉ ተጨማሪ ምርመራ መደረግ አለበት” ብለዋል፡፡

በሽታው ተላላፊ በመሆኑ አስታማሚዎች እንዳይተላለፍባቸው በመፍራት የሚያደርሱት የመገለል ስነ ልቦና ጫና ለመቅረፍ በቂ አየር ዝውውር እንዲኖር በማድረግ ህሙማኑን መንከባከብ ያስፈልጋል ነው ያሉት ስፔሻሊስቱ ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም