እንግሊዝ በአፍሪካ ለታዳሽ ኃይል ልማት የሚውል 30 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
እንግሊዝ በአፍሪካ ለታዳሽ ኃይል ልማት የሚውል 30 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ አደረገች
አዲስ አበባ ካቲት 29/2011 እንግሊዝ በአፍሪካ ታዳሽ ኃይልን ለማስፋፋት የሚያግዝ 30 ሚሊዮን ፓውንድ ተጨማሪ ድጋፍ ማድረጓን አስታወቀች።
የእንግሊዝ መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ሃሪየት ባልድዊን ትላንት ለንደን ላይ እንደተናገሩት ብዛት ያላቸው አፍሪካውያንና በአህጉሪቱ የሚሰሩ ኩባንያዎች ከታዳሽ ኃይል ልማቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ኢንጅነር ስለሺ በቀለን ጨምሮ በርከት ያሉ አፍሪካውያን ሚኒስትሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የተደረገው ድጋፍ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አፍሪካውያን ታዳሽ ኃይልን እንዲያገኙና ኑሯቸቸውን እንዲያሻሻሉ እንደሚያግዛቸውም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን ቶን የካርቦን ልቀትን ለማስቀረትም አንደሚያግዝ የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አመልክቷል።
የእንግሊዝ መንግስት ቀደም ብሎም ለታዳሽ ኃይል ልማት የሚውል 359 ሚሊዮን ዶላር ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ በመመደብ እየሰራ ይገኛል።
ድጋፉ ይፋ የተደረገው እንግሊዝ ባለፈው ዓመት በተባበሩት መንግስታት የአየር ለውጥ ጉባኤ ላይ ከሰሃራ በታች ለሚገኙ 40 የአፍሪካ አገራት የታዳሽ ኃይል ምርቶችን በማቅረብ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌከተሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የገባችውን ቃል ተከትሎ ነው።
የእንግሊዝ የግል ኩባንያዎች በአፍሪካ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ በንቃት እየተሳተፉ ሲሆን በኢትዮጵያም በኮርቤቲ የእንፋሎት ኃይል ልማት ላይ በመሳተፍ ላይ ነው።