ቀጥታ፡

ጠንካራ መንግስታዊ መዋቅር በመዘርጋት ለክልሉ ህዝብ የላቀ ተጠቃሚነት እሰራለሁ---ዶክተር አምባቸው መኮንን

ባህርዳር የካቲት 29/2011 ጠንካራ መንግስታዊ መዋቅር በየደረጃው በመዘርጋት ለክልሉ ህዝብ የላቀ ተጠቃሚነት በትጋት እንደሚሰሩ አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን አስታወቁ።

በክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ዛሬ የተሾሙት ዶክተር አምባቸው  ባደረጉት ንግግር "  ውስብስብ ችግሮች ባሉበት ወቅት ርዕሰ መስተዳደር ሆኜ ብሾምም የክልሉ ህዝብ የጣለብኝን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት ለማገልገል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ እንደነበር አስታውሰው  በተካሄደው የህዝብ ግፊትም ለአሁኑ ለውጥ መብቃት እንደቻለ ገልጸዋል። 

የክልሉን የመልማት ዕድል የሚጎትቱ የመንገድና መሰል የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ችግሮችን የሃብት ብክነትን በሚቆጥብ መልኩ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለህዝቡ ጥቅም እንዲውሉ የሚሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

እሳቸው አንዳሉት በክልሉ ለሚገኘው ስራ አጥ ወጣት የስራ ዕድል ለመፍጠርና ሃብትን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ ተግባራትም በልዩ ትኩረት ይሰራል፡፡

ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማትና ሌሎችንም የልማት ስራዎች  በቀጣይ ትኩረት አድርገው ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል እንደሚገኙበት አመላክተዋል።

ህዝቡም ህግንና ስላሙን እንዲያስከብር፣ የፍትህ መጓደልና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ የአካባቢያቸው መልሶ እንዲቋቋሙ ማድረግም ሌሎቹ ስራዎቻቸው እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

በተለይም የአማራ ህዝብ ወንድም ከየሆነው የትግራይ ህዝብ ጋር የቀደመ አንድነቱ እንዲጠናከር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የክልሉ ከተሞች በፕላን እንዲመሩ፣ አካታች ልማቶች የሚከናወንባቸውና አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባቸው እንዲሆኑ ህዝቡ ከክልሉ መንግስት ጎን ሆኖ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣቶች ለነፃነትና ለህግ የበላይነት መከበር የከፈሉት መስዋዕትነት እንዳይቀለበስ  በአንዳንድ አካባቢዎች የህዝቡን ሰላም የሚያውኩ በመኖራቸው ሰላም እንዲሰፍን ግንባር ቀደም ሆነው እንዲሰሩም መልዕክታቸውን አስተላፈዋል፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም የሚለያዩ አስተሳሰቦችን ወደጎን በመተው ሀገራዊ ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን የሚመግቡ አስተሳሰቦች ላይ እንዲያተኩሩም አሳስበዋል።   

በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች ወንድማማችነትን ለማጎልበትና  ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል።   

በክልሉ በየደረጃው ያለውን መንግስታዊ አደረጃጀትን ፈትሾ  ጠንካራ መዋቅር በመዘርጋትም የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰሩም ዶክተር አምባቸው አስታውቀዋል።

ተሰናባቹ የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም መስክ የተቀየሱ የልማት አቅጣጫዎች እንዲፈፀሙ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ህዝብ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመረረ ትግል ውስጥ የገባው በተደራጀው የአፈና ቡድን በተፈፀመበት ግፍና በደል ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን ለውጡ እንዲመጣ  ነው፤ ለዚህም ሰርቷል።    

አዲስ አይነት የምዝበራ ቡድን እንዳይፈጠርም ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በመሆን በቀጣይ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የክልሉ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር ለዘመናት የተዘራውን የጥላቻ ፖለቲካ በተስተካከለ አቅጣጫ በማስተካከል  አዲሱ ርዕሰ መስተዳደር በቀጣይ መስራት አለባቸው ብለዋል።

"ውስጣዊ አንድነት የሌለው ህዝብ ቁጥሩ ቢበዛ ጥቅም የለውም፤  ወንዝ ሊያሻግር የሚችል ጠንካራ አንድነት በቀጣይ ፈጥረን መንቀሳቀስ ይኖርብናል " ሲሉም አቶ ገዱ አሳስበዋል።

የአማራ ህዝብ  የሚናፈሰውን ወሬ ወደጎን በመተው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አመልክተዋል።

በተለይ ግንኙነቱ በየጊዜው እየተሸረሸረ የመጣውን የትግራይና የአማራ  ህዝቦች ወደቀደመ አንድነታቸው እንዲመጡ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

"አጎራባች ከሆኑ ከኦሮሞና ከሌሎች ክልል ህዝቦች ጋር የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ትስስም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል "ብለዋል።

አቶ ገዱ ባለፉት አምስት ዓመታት ከጎናቸው በመሆን ድጋፍ ላደረጉላቸው ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም