በፓርኩ የሐርቨንድ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሥራውን ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በፓርኩ የሐርቨንድ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሥራውን ቀጥሏል
ሐዋሳ የካቲት 29/2011 በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሐርቨንድ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሠራተኞች ሥራ መቀጠሉን ፓርኩ አስታወቀ፡፡
የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ ለኢዜአ እንደገለጹት ከፋብሪካው ሶስት የማምረቻ ሼዶች የአንደኛው 500 ሠራተኞች ባቀረቡት ቅሬታ ለአንድ ቀን የተቋረጠው ሥራ እንዲቀጥል ተደርጓል።
ሠራተኞቹ ሥራቸውን ለማቆም ምክንያቶቻቸው የደሞዝ ማነስና የመብት ጥያቄዎች እንደነበሩም አስታውሰዋል።
"የሠራተኞቹን ቅሬታ ለመፍታት የፓርኩ አስተዳደር የሰራተኞች ዩኒትና ከደቡብ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተወከሉ አካላት በተገኙበት ከካምፓኒው ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል"ብለዋል፡፡
የካምፓኒው ባለቤቶች በሚያስተካክሏቸውና በመንግሥት የሚፈቱ ጉዳዮች ተለይተው ስምምነት ላይ በመደረሱ የተቋረጠው ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
የፋብሪካው የሁለቱም ፈረቃዎች ሥራተኞች በሥራቸው ላይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ፍጹም፤ በፓርኩ በሥራ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚፈቱበት አሰራር መኖሩን ጠቁመዋል።
በክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነትዳይሬክተር አቶ አስረስ ግዛው "ሠራተኞቹ ባነሷቸው የደሞዝ ክፍያ አነስተኛነት፣ በሠራተኞች አያያዝ፣ ሕክምናና ምግብ ጨምሮ ሌሎች የመብት ጥያቄዎች ላይ ውይይት ተደርጓል" ብለዋል ።
ሠራተኞቹ በዋናነት ያነሱት የደሞዝ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ ስለሚሻ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯና ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር ነገ ውይይት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
"በሠራተኛ አያያዝ የተነሳው የአሰሪዎች የሥነ ምግባር ጉድለት መፈተሽ እንደሚገባው ከካምፓኒ ኃላፊዎች ጋር ተስማምተናል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሕክምናን በተመለከተ ኩባንያው በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነርሶችን ቀጥሮ አገልግሎት እንዲጀምር እንዲሁም የምግብ ጥራት ችግርን የሚፈታ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንዲሰራ ከመግባባት ላይ መደረሱንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 22 ፋብሪካዎችና 52 ሼዶች ያሉ ሲሆን ፣25ሺህ ሠራተኞች ይገኛሉ።