"ጠንካራ አገር ያለ ጠንካራ ሴት አይገነባም" - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2011 "ጠንካራ አገር ያለ ጠንካራ ሴት አይገነባም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን 'ማርች 8' በኢትዮጵያ ለ43ኛ ጊዜ በአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተከብሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የማህበረሰብ ግማሽ አካል የሆኑትን ሴቶች በአገር ልማት ላይ ሳያሳትፉ እድገትን ማሰብ አይቻልም።

ሴቶች የማህበረሰብ ተሸካሚ ምሰሶዎች በመሆናቸው ጠንካራ ሴቶች ከሌሉ ጠንካራ አገር መገንባት እንደማይቻል ነው የተናገሩት።

ሴቶች ያላቸውን ሚና ተረድተው ሰላማዊና ፍቅር የሰፈነባት አገር በመገንባት ሂደት የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቀናጀ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መርሃ-ግብር ዳይሬክተር ሚሼል ሲዲቤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ማርች ስምንትን ለማክበር ትክክለኛ ቦታ መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሴቶችን ወደ አመራር ሰጪነት በማምጣት ረገድ ያከናወነችውን ተግባር ለሃሳባቸው በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ለዚህ ስኬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን አመስግነዋል።

በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ በአማካኝ 460 ሴቶች በኤች አይ ቪ ቫይረስ እንደሚያዙ ጠቁመው፤ ይህንና መሰል የሴቶችን ችግር ለመቅረፍ ብዙ ርቀት መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

"የተለያዩ የስደተኛ ካምፖችን ተዘዋውሬ ስመለከት በዜጎች መፈናቀል ዋነኛ ተጎጂዎች ሴቶች መሆናቸውን ማረጋገጥ ችያለሁ" ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፈቂ ማህመትን በመወከል ንግግር ያደረጉት የህብረቱ የፖለቲካ ጉዳይ ኮሚሽነር ሚናታ ሳማቲያ ናቸው።

ኢትዮጵያ እነዚህ ስደተኞችን በሰላም በመቀበል ረገድ በአብነት የምትጠቀስ አገር መሆኗንም አክለዋል።

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው በየቀኑ ከሶስት ሴቶች አንዷ ለጾታዊ ጥቃት ትጋለጣለች።

በሴቶች ላይ ከሚፈጸሙ ግድያዎች መካከል ደግሞ 38 በመቶ የሚሆነው በፍቅረኞቻቸውና የትዳር አጋሮቻቸው የሚፈጸም ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም