ቀጥታ፡

በመቀሌ ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ነዋሪዎች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በጋራ አከበሩ

መቀሌ የካቲት 29/2011 በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አየር ሃይል ምድብ ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የመቀሌ ከተማ ሴቶች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን /ማርች 8/ በተለያዩ ዝግጅቶች በጋራ አከበሩ፡፡

በዓሉ በዓለም አቀፍ ለ108ኛ፣ በአገር አቀፍ ደግሞ ለ43ኛ ጊዜ "ለሴቶች ሰላምና አንድነት ሁለገብ ትኩረት እንስጥ! " በሚል መሪ ቃል ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተከብሯል፡፡

የበዓሉ ተሳታፊዎች በዓሉን በስፖርት፣ በፓናል  ውይይትና በሌሎች የመዝናኛ ዝግጅቶች  አክብረውታል፡፡

በሰሜን እዝ አየር ኃይል ምድብ ሴቶች አባላት ተወካይ  ሻለቃ ንግስት ከበደ "ባለፉት ዓመታት የሴቶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች ተከናውነዋል" ብለዋል፡፡

ይሄም  ሴቶች በሁሉም የስራ መስኮች ከፍ ብለው እንዲታዩ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የመቀሌ ከተማ ሴቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ  ዛህራ መሐመድ ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማጠናከር በዕድገት ተኮር የልማት ስራዎች መሰማራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ሴቶች በሁከትና ግርግር ግንባር ቀደም ተጠቂ መሆናቸውን ያስታወሱት ኃላፊዋ፣ የሕግ የበላይነትን እንዲረጋገጥ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በመቀሌ ሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ በተከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን /ማርች8/ በዓል ከ600 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም