የባህር ዳር የእሳት አደጋ ተጎጂዎች መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር የእሳት አደጋ ተጎጂዎች መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጠየቁ
ባህርዳር የካቲት 29/2011 በባህር ዳር ከተማ በደረሰው የእሳት አደጋ ንብረታቸው የወደመባቸው ሰዎች መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጠየቁ፡፡
የከተማው እሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪ አደጋውን ለመመከት በቂ ጥረት አላደረገም ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የከተማው ከንቲባ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከዛሬ ጀምሮ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ተጎጂዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት መንግሥት ከደረሰባቸው ጉዳት የሚቋቋሙበትን ጊዜያዊና ዘላቂ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል።
ጉዳቱ ከደረሰባቸው ሰዎች ማከከል አቶ ሔኖክ ማሩ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት በተከሰተው አደጋ የመኖሪያ ቤታቸው ከነሙሉ ዕቃው መውደሙንና ለከብቶች መኖ መግዣ አስቀምጠውት የነበረው 27 ሺህ ብርም መቃጠሉን አስታውቀዋል፡፡
በተከሰተው የእሳት አደጋም አምስት ቤተሰቦቻቸውንና የእርባታ ላሞቻቸውን ከአደጋው ማዳናቸውን ተናግረዋል፡፡
አደጋው ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ የከተማው ሕዝብ በተለይም ወጣቱ እሳቱን ለማጥፋት መረባረቡን የተናገሩት ተጎጂ፣የከተማው እሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪ እገዛ ግን አናሳ ነበር ብለዋል፡፡
ክስተቱ ቤት አልባ ስላደረጋቸው መፍትሄ እንዲፈለግላቸውም ጠይቀዋል፡፡
''በእሳት አደጋው ሙሉ ንብረቴ ወድሟል፤ የተረፈ እቃ የለም'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ እመዋ ምትኩ ናቸው፡፡
''በዘበኝነት ተቀጥሬና በትርፍ ሰዓቴ በጉልት እንቁላልና ቆሎ ሸጬ አምስት ቤተሰቦችን ከማስተዳደር አልፎ ያፈራሁት ሃብትና ንብረት በእሳት አደጋው ወድሟል''ሲሉም ጉዳታቸውን ይገልጻሉ።
የከተማው የእሳት አደጋ ተሽከርካሪ ዘግይቶ መምጣቱን ያስታወሱት ወይዘሮ እመዋ፣ አገልግሎት የሰጠውና ቆሞ ይጠብቅ የነበረው ትላልቅ ሆቴሎችን ነበር ሲሉ ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ከችግሩ ለመውጣት እንዲችሉ መንግሥት ፈጥኖ ሊያግዘን ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
''በሽተኛ ባለቤቴን ታቅፈው በማውጣትና ስድስት ልጆቼን ከእሳት አደጋው የታደጓቸው ወጣቶች ናቸው'' ያሉት በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ወይዘሮ ልይሽ ነጋ ናቸው፡፡
ከአደጋው የተረፈ ንብረት ስለሌለኝ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሄ ይፈለግልኝ ብለዋል፡፡
የከተማው ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ በበኩላቸው አደጋው በተነሳበት አካባቢ ያሉት ቤቶች አብዛኛዎቹ ተቀራርበው ከእንጨት የተሰሩ በመሆናቸው የመከላከል ሥራውን አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ፤ ጉዳቱንም የከፋ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡
በአደጋው የደረሰውን የጉዳት መጠን ኮሚቴ ተቋቁሞ እያጣራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጸጥታና የሎጀስቲክስ ኮሚቴም ተቋቁሞ ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማድረግ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡
ለተጎጂዎቹ ጊዜያዊ መፍትሄ የመፈለግ ሥራ ዛሬ ይጀምራል ያሉት ከንቲባው፣ በሚመጣው መረጃ መሠረትም በቀጣይ የሚደረግ ድጋፍ ይገለጻል ብለዋል፡፡
ለአብነትም የአማራ ክልል ስፖርት ከሚሽን 100 ፍራሾች መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ከማህበረሰቡ ገንዘብ ለማሰባሰብም የባንክ አካውንት ለመክፈት ሂደቱ መጀመሩን ገልጸዋል።
በእሳት አደጋው የመቁሰል አደጋ ያጋጠማቸው ሰዎች ካሉም በባህር ዳር ጤና ጣቢያ በነፃ እንዲታከሙ ተመቻችቷል፡፡የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም የሕክምና እርዳታ ያደርጋል ብለዋል፡፡
አደጋውን ለመቆጣጠር የከተማው ሕዝብና በተለይም ወጣቶችና የፀጥታ ኃይሎች ላደረጉት ርብርብም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የከተማው የእሳት አደጋ ተሽከርካሪ ወደ አሰጋው ሥፍራ የደረሰወ ዘግይቶ ነው ለተባለው ቅሬታ በሰጡት ምላሽም ትክክል እንዳልሆነና ቅሬታ የቀረበበት በልመና የመጣው የአየር ኃይል እሳት አደጋ ተሽከርካሪ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ተጎጂዎችን መልሶ ለማደራጀትና ወደ ቀደመ ህይወታቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረትም ድጋፉን እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
የከተማዋ ወጣቶች ለተጎጂዎቹ ጊዜያዊ መጠለያ ድንኳኖች ሲጥሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ተመልክቷል፡፡