ትውልዱ በንግግርና በውይይት የመግባባት ልምዱን ሊያዳብር ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ በንግግርና በውይይት የመግባባት ልምዱን ሊያዳብር ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ የካቲት 29/2011 በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈንና በዘላቂነት ግጭቶችን ለማስወገድ የትውልዱን በንግግርና በውይይት የመግባባት ልምድ ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አንድ ምሁር ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶክተር ታፈሰ ኦሊቃ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ብሔርን መሰረት አድርገው የተሰሩ ስራዎች አንድነትን ከማጠንከር ይልቅ የሚከፋፍሉ ነበሩ።
በዚህም ጎጠኝነት መንገሱን የተናገሩት ዶክተር ታፈሰ “የህዝቡ አብሮነት ተሸረሸረ፤ አገሪቷ በቋንቋ የፌዴራል ስርዓት ተሸነሸነች” ሲሉ ገልጸዋል።
ዜጎች ከክልል ወደ ክልል ተዘዋውረው ለመስራትና ሀብት ለማፍራት ሲንቀሳቀሱ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የማየት ዝንባሌዎች መስፋፋታቸውንም ተናግረዋል።
ይህም የህዝቡን የመቻቻልና የአንድነት እሴቶች በመሸርሸረ በአገሪቱ ግጭቶች ለመከሰታቸው መንስኤ መሆኑን ገልጸው ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የትውልዱን በንግግርና በውይይት የማመን ልምድ ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ነው ዶክተር ታፈሰ የገለጹት።
በአገሪቱ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ ተቋማዊ መልክ እንዲኖረው ማድረግና መንግስት ከህዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የብሔራዊ እርቅ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ በበኩላቸው ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስወገድ ሕብረተሰቡ ራሱን የችግሩና የመፍትሄ አካል ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።
"ሕብረተሰቡ ሌሎች ወገኖችን ብቻ እንደ ጥፋተኛ ከመመልከት ይልቅ ወደ ራሱ ቢመለከት ሰላምና መግባባትን ለመፍጠር ግማሽ መንገዱን ተጉዟል ማለት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
“በጓሯችን ዘርተን ያሳደግነውን የግጭት ዕጽ፣ እርስ በእርስ ያለመከባበር፣ እኔ ነኝ የምበልጠው፣ የእገሌ ድምጽ ለምን ይሰማል እኔ እያለሁ የሚል ስር የሰደደ ካንሰር ለማጥፋት ትልቁ የእኔ ድርሻ ምንድን ነው?“ ብለን መጠየቅ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ሙሉዓለም በበኩላቸው በአገሪቱ የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ የመጡ በመሆኑ እንዲያንሰራሩ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
አቶ መላኩ እንደተናገሩት በአገሪቱ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ለመለየት የሚያስችል ጥናት በማድረግ መከናወን ያለባቸውን ስራዎች ለመስራትና መልካም ተሞክሮዎችን ለማጠናከር የሚያስችል ስትራቴጂ በማዘጋጀት መስራት ያስፈልጋል።
የሰላም ፖሊሲ ማዘጋጀትና የሰላም አስፈላጊነትና ችግሮችን በሰላም መፍታት ላይ ያተኮሩ ትምህርቶችን በስርዓተ ትምህርቱ ላይ ማካተት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከሚያስችሉ መፍትሄዎች መካከል አንስተዋል።
ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ ተቋማትን ማጠናከርና ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ስለ ሰላም እንዲሰሩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አክለዋል።
ሕብረተሰብ ሰላሙን ለመጠበቅ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ያስገነዘቡት አቶ መላኩ “ፖሊስ ሁልጊዜ ሰላሜን ይጠብቃል ማለት አይቻልም ሁሉም ሰላሙን በንቃት መጠበቅ አለበት" ብለዋል።
ሰላም ለማስጠበቅ የሚያችሉ ጥናቶችን የማሰበሳብና ስራ ላይ እንዲውሉ ለማስቻል እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልጸዋል።