ቀጥታ፡

"ሴቶች ፍትሃዊ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው የስኬታቸው ጣርያ ሰማይ ነው" -ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2011 "ሴቶች ፍትሃዊ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው የስኬታቸው ጣርያ ሰማይ ነው" ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት ትናንት ምሽት በስካይላይት ሆቴል፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አለም አቀፍ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚመራ በረራ ወደ ኖርዌይ ኦስሎ የሚያደግበትን ሥነ-ሥርዓት በከፈቱበት ወቅት ነው።

አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ስዊድን ስቶኮልም እና ኖርዌይ ኦስሎ የሚደረገውን በረራ ከቴክኒሻን እስከ አውሮፕላን አብራሪ በሴቶች የሚመራ መሆኑ ተገልጿል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር የዓለም ጸጋይ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያምን ጨምሮ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በዚህ  ወቅት ፕሬዝዳንቷ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አለም አቀፍ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚመራ በረራ መደረጉ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ሰንደቅ ተሸክሞ በአየር ላይ የሚበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዲፕሎማቶች በላይ አገሪቱን ማስተዋወቁን ገልፀው በሴቶች የሚመራ በረራ ማድረጉ ደግሞ አገሪቱን ለዓለም ህዝብ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያስተዋውቃት አስረድተዋል።

"ሴቶች ፍትሃዊ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው የስኬታቸው ጣርያ ሰማይ ነው" ብለዋል ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በበኩላቸው በሁሉም የበረራ ዘርፍ ብቁ ሴቶች በተቋሙ መኖራቸውና አሁን የሚደረገው በረራም ሙሉ በሙሉ በሴቶች በመመራቱ ኩራት እንደተሰማቸው ገልፀዋል።

ለአየር መንገዱ ስኬት ሴቶች ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በመሆኑ የሚደረገው በረራ የሴቶቹን አስተዋጽኦ እውቅና የሚሰጥ ነውም ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ።

አየር መንገዱ በሳምንት አምስት ጊዜ በ787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በስዊድን ስቶኮልም አድርጎ ኦስሎ ኖርዌይ የሚበር ሲሆን አሁን የተደረገው ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚመራ በረራ ቀደም ሲል ከተደረጉት ባንኮክ፣ ኪጋሊ፣ ሌጎስና ቦነስአይረስ ቀጥሎ አምስተኛው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም