ቀጥታ፡

ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስኬት የቀድሞው ፕሬዝዳንት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው--ዩኒቨርሲቲው

ጎንደር የካቲት 28/2011 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት የነበሩት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በፈቃዳቸው ከሃላፊነት መልቀቃቸውን የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት አስታወቁ።

ፕሬዝዳንቱ ኃላፊነታቸውን የለቀቁት በአሜሪካን ሀገር ኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ አፍሪካ የጤና ኢንስቲትዩት ረዳት ዳይሬክተር በመሆን ባገኙት ከፍተኛ የስራ ሃላፊነት መሆኑም ተመልክቷል።

ላለፉት 13 አመታት በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ሲያገለግሉ የነበሩት ዶክተር ደሳለኝ ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ለደረሰበት ለውጥና እድገት አስተዋጽኦ ካበረከቱ ምሁራን ግንባር ቀደም እንደነበሩ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንቱ ዶክተር አስራት አጸደወይን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላስመዘገባቸው ተጨባጭ ለውጦች የዶክተር ደሳለኝ መንገሻ ያልተቆጠበ የአመራር ድጋፍና ክትትል ወሳኝ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

“አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲከፈቱ፤ ሁለተኛና ሶስተኛ የዲግሪ መርሃ ግብሮች በአይነትም ሆነ በብዛት እንዲጨምሩ በማድረግ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በዩኒቨርሲቲው ለተመዘገበው ለውጥ የዶክተር ደሳለኝ ሚና ከፍተኛ ነበር” ብለዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲን በሀገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመወዳደር በተከታታይ ግንባር ቀደም በማድረጋቸው የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት በየአመቱ በሚዘጋጀው የጥራት ውድድር ላይ ለተከታታይ ሶስት አመታት በአንደኛ ደረጃ አሸናፊ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአሜሪካን ሀገር ኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ አፍሪካ የጤና ኢንስቲትዩት ረዳት ዳይሬክተር በመሆን ባገኙት ከፍተኛ የስራ ሃላፊነት ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንትነት እንደለቀቁም ምክትል ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል።

“ፕሬዘዳንቱ ላለፉት 13 አመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በታታሪነትና በላቀ ምሁራዊ የአመራር ሰጪነት ላስመዘገቡት ውጤት ዩኒቨርሲቲው ተገቢውን ላቅ ያለ አውቅና ይሰጣል” ብለዋል፡፡

አዲስ የተመደቡበት የስራ ሃላፊነት የተሳካ እንዲሆን የዩኒቨርሲቲው አመራርና ማህበረሰብ መልካም ምኞቱን እንደሚገልጽም ምክትል ፕሬዘዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

ከዩንቨርሲቲው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ዶክተር ደሳለኝ በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ከመምህርነት ጀምሮ በአካዳሚክ ፕሮግራም ኦፊሰርነት፤ በአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንትና እስከ ለቀቁበት ጊዜ ድረስም በፕሬዘዳንትነት አገልግለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም