ታዳሽ ኃይል ላይ መስራት ለዘላቂ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ታዳሽ ኃይል ላይ መስራት ለዘላቂ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተባለ
አዲስ አበባ የካቲት 28/2011 ኢትዮጵያ ተለዋዋጭ የአየር ንብረት ለውጥ የማያሰናክለው የኃይል አቅርቦት እንዲኖራት ባላት እምቅ ታዳሽ ኃይል ላይ መስራት እንዳለባት ጥናት አመለከተ።
የኢትዮጵያን ታዳሽ ኃይል ሽግግር ለማፋጠን በሚል ሬስ ፎር አፍሪካ የተባለ አለማቀፍ ተቋም ያዘጋጀው የታዳሽ ኃይል አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በአውደ ጥናቱ በታዳሽ ኃይል ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ያላትን አቅምና አቅሙን ለመጠቀም ያላስቻሉ ችግሮች ላይ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በጥናቱ እንደተገለፀው በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የአገሪቱ ኃይል የሚመነጨው ከውሃ ሲሆን ከነፋስ፣ ከጂኦተርማልና ከፀሃይ የሚገኙ ያልተጠቀመችባቸው ታዳሽ ኃይሎች መኖራቸውን ጥናቱ አመላክቷል።
እነዚህን እምቅ አቅሞች ወደ ስራ ለማስገባትና የኃይል ምርት ለማሳደግ የመንግስትና የግል ዘርፍ ትብብር ወደ ስራ መግባት እንዳለበትም ነው የተመለከተው።
የውሃ መጠን የሚቀንስባቸውንና በድርቅ ምክንያት ሊቀንስ የሚችልን ከውሃ ኃይል የሚገኝ ኃይል ለማገዝም እነዚህ ታዳሽ ኃይሎች ጠቀሜታቸው የጎላ እንደሚሆን ነው የተብራራው።
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ኃይል በመውሰድ ላይ ያሉም ይሁኑ ፍላጎቱ ላላቸው አገራት ያልተቆራረጠና እድገት ያለው ኃይል ለማቅረብ ታዳሽ ኃይሎች ወደ ኃይል መስመሩ መግባት እንዳለባቸው ተገልጿል።
በሌላ በኩል መንግስት አገሪቱ ያላትን የኃይል አቅም ለመጠቀም ካለው የካፒታል እጥረት ሳቢያ የግል ዘርፉ ኃይል በማመንጨት ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ እንደሚሆን ነው ከውይይቱ የተንፀባረቀው።
ለማሳደግ ተጨማሪ ታዳሽ ኃይሎችን ወደዋናው ኃይል ስርዓት ማስገባት ከተቻለ የተሻለ ገቢ ለአገሪቱ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ጥናቱ አሳይቷል።
አሁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያቀደው የማሰራጫ መስመር ማስፋፊያም ታዳሽ ኃይሎቹን ከመስመሩ ለማገናኘት አስተዋጽኦ የሚያደርግ እንደሆነም ተንፀባርቋል።
የኢትዮጵያ ኤለሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ለኢዜአ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም የግል ዘርፉ በነዚህ መስኮች እንዲሰማራ የሚያስችል ፖሊሲና የአሰራር ስርዓት መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
በመንግስት የተጠኑ የኃይል ፕሮጀክቶችንም ይሁን ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች አጥንተው በሚያመጡት ፕሮጀክት መሰረት ወደ ስራ እንዲገባ መንግስት በሩን ክፍት ማድረጉንም አክለው ነግረውናል።
ክፍት ተደርጓል በተባለው የአሰራር ስርዓት የግሉ ዘርፍ ኃይል አምርቶ ለመንግስትም ይሁን ለግል ዘርፉ መሸጥ እንዲችል የሚያስችል ነው ብለዋል።
የመጀመሪያው የባለሃብት ጥሪ ላይ ከ140 በላይ ተጫራቾች የመጡ እንዳሉ የገለፁት ዶክተር አብርሃም የአሰራር ስርዓቱ መዘጋጀቱ ደግሞ ሌሎች ባላሃብቶችን ፍላጎት እነደሚያነሳሳ ገልፀዋል።
ኢኔል የተባለ የመተሃራ ፕሮጀክት ወደስራ የገባ ሲሆን በቅርቡም የገንዘብ ሚኒስቴር ለጨረታ ያዘጋጃቸው ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል።
ያለው የኃይል አማራጭ እንኳን በመንግስት የግል ዘርፉም ቢገባ አሟጦ ሊጠቀመው የማይችል ሰፊ ሃብት እንዳለ ነው ዶክተር አብርሃም የገለጹት።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና እንዳሉት ከታዳሽ ኃይል የሚገኝ እምቅ ኃይል ቢኖራትም ዘርፉ ወደ ኃይል መስመር ሳይገባ እስካሁን ቆይቷል።
ችግሩን ለመቅረፍ በመንግስት ብቻ የማይቻል በመሆኑ በመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የጋራ ስራ ላይ የወጣውን አዋጅ መሰረት በማድረግ የውጪና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲሰማሩ እየተሰራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ተጨማሪ ታዳሽ ኃይልን ወደ ኃይል ስርዓቱ ለማስገባት እየሰራች ሲሆን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2030 ከውሃ የምታመነጨውን ኃይል በ10 በመቶ ለመቀነስ ትሰራለች ብለዋል።