ኢትዮጵያ በጤና ፖሊሲዋ ላይ ማሻሻያ ልታደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጤና ፖሊሲዋ ላይ ማሻሻያ ልታደርግ ነው

አዲስ አበባ የካቲት 28/2011 ኢትዮጵያ በጤና ፖሊሲዋ ላይ ማሻሻያ ልታደርግ መሆኑን የጤና ሚንስትሩ ዶክተር አሚር አማን ተናገሩ።
የጤና ሚኒስቴር ከፌዴራልና ክልሎች ከተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና የስራ ሃላፊዎች ጋር አዲስ በተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲ ዙሪያ ምክክር አካሂዷል።
ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት እስካሁን ሲተገበር የነበረውና መከላከልን መሰረት ያደረገው ፖሊሲ ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ውጤታማ ነበር።
አሁን በመተግበር ላይ ያለው የአገሪቷ የጤና ፖሊሲም ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 25 ዓመታት አገልግሏል።
ይሁን አንጂ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2016 ጀምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና አደጋዎች 51 በመቶ መጨመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በመሆኑም በዜጎች ላይ እየተከሰተ ያለው የሞት፣ የአካልና የአእምሮ ጉዳቶች እየጨመረ በመምጣቱ የአገሪቷን የጤና ፖሊሲ በማሻሻል ችግሩን መግታት ማስፈለጉን ሚንስትሩ ተናግረዋል።
ፖሊሲው የጤናው ዘርፍ ገቢውን በራሱ እንዲደግፍ ለማስቻልና ከመንግስት ጎን በመሆን የፋይናንስ ፍላጉቱን በማሟላት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግም ያግዛል ተብሏል።
ከውጭ አገራት በሚገኝ እርዳታና ብድር ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆን ለማስቻልም የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ይሆናል ነው ያሉት ዶክተር አሚር።
በእለቱ የረቂቅ ፖሊሲውን ይዘት የሚዳስስ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት በሚኒስቴሩ ዴሊቬሪ ክፍል ባለሙያ አቶ ካህሱ በክረፅዮን እንዳሉት አገሪቱ ከደረሰችበት የማህበራዊና ኢኮኖሚ ለውጦች አንፃር ፖሊሲውን መከለስ አስፈልጓል።
የህዝቡን የጤና ተደራሽነትና አገልግሎት የሚያሟላ፣ ከእድገቱ ጋር የሚጣጣም ፍትሃዊና ጥራቱን የጠበቀና የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግም እንዲሁ።
እንደ አቶ ካህሱ ገለፃ ዜጎች በጤና ችግር ምክንያት ለኢኮኖሚ ቀውስ በማይዳረጉበት መልኩ ምቹና የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል መስራት ያስፈልጋል።
በመሆኑም በመሻሻለው ፖሊሲ የእናቶችና ህጻናትን ሞት መቀነስ፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መቀነስ፤ በአደጋ ሳቢያ የሚከሰትን ሞትና የአካል ጉዳት እንዲሁም የአእምሮ መቃወስን መከላከልን ያካትታል።
የመድሃኒት፣የህክምና መሳሪያ አቅርቦትና አጠቃቀም ላይ በማሻሻል በግብአት እጥረት ምክንያት የሚከሰትን ውስብስበ አሰራር ለማስቀረትም አዲስ አሰራር ያስቀምጣል።
በተጨማሪም የባህል ህክምናን በጥናትና ምርምር በማጎልበት ለህብረተሰቡ ጤና አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማስቻል ሌላው በፖሊሲው የተካተተ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሚሻሻለው ፖሊሲ በአጭር ግዜ ውስጥ ጸድቆ ተግባራዊ እንዲደረግ በመጠየቅ በጤናው ዘርፍ ለሚነሱ ቅሬታዎችና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልል ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ያለው የጤና ተደራሽነት እየተሻሻለ ቢመጣም በቂ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያ አቅርቦት አለመኖሩን ጠቅሰው በቀጣይ ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።
አዲሱ ረቂቅ የጤና ፖሊሲ በቀጣይ ተከታታይ ውይይቶች ተካሂደውበት ግብአቶች ከተሰበሰቡበት በኋላ ለሚንስትሮች ምክር ቤት የሚቀርብ ይሆናል።