ኢትዮጵያ ለመጀመሪያው ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ቦውሊንግ ሻምፒዮና ትሳተፋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያው ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ቦውሊንግ ሻምፒዮና ትሳተፋለች
አዲስ አበባ የካቲት 28/2011 ኢትዮጵያ ከመጋቢት 9 እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት ለመጀመሪያው በሚካሄደው የአፍሪካ ቦውሊንግ ሻምፒዮና ትሳተፋለች።
የአፍሪካ ቦውሊንግ ፌዴሬሽን በበላይነት በሚመራው ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴራሊዮን፣ ሲሸልስ፣ ግብጽ፣ ናይጄሪያና ቱኒዚያ ይሳተፋሉ።
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በወንድ ስምንት፣በሴት አራት በድምሩ 12 ተወዳዳሪዎችን ታሳትፋለች።
የኢትዮጵያ ቦውሊንግ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ምንሊክ ሀብቱ ለኢዜአ እንደገለጹት ተወዳዳሪዎቹ ለሻምፒዮናው ቅድመ ዘግጅት ይረዳቸው ዘንድ ከየካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮ በላፍቶ ሞል ልምዳዳቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።
አሰልጣኝ ጌታቸው አለኸኝና ይጥና ተፈራ ለተወዳዳሪዎቹ በአወራወር፣ ትኩረትን መሰብሰብ፣ የውድድር ዝግጁነትና ሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ተወዳዳሪዎቹ ከታህሳስ እስከ የካቲት 2011 ዓ.ም በሻምፒዮናው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ከተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቦውሊንግ ሻምፒዮና የተመረጡ ናቸው።
ኢትዮጵያን ተወዳዳሪዎች በአህጉራዊው ውድድር መሳተፋቸው አቅማቸውን ለማሳዳግና ልምድ ለመቅሰም እንደሚያግዛቸውም ነው አቶ ምንሊክ ያስረዱት።
ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ 15 ልዑካን የያዘው የኢትዮጵያ የቦውሊንግ ቡድን መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚያቀናም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም የአፍሪካ ቦውሊንግ ፌዴሬሽን በግብጽ ሲመሰረት መስራች አባል ከሆኑት አገሮች መካከል እንዷ ነች።
የቦውሊንግ ስፖርት በኢትዮጵያ መዘውተር ከጀመረ 50 ዓመታትን እንዳስቆጠረና ላለፉት አራት አስርት ዓመታት በተለያዩ ዓለም አቀፍ የቦውሊን ውድድሮች ላይ ተካፋይ እንደነበረች መረጃዎች ያመለክታሉ።
የቦውሊንግ ስፖርት በእንጨት በተሰራ ወለል ኳስ በመወርወር የተዘጋጁ ኢላማዎችን (ፒኖችን) በመጣል ነጥብ በማስቆጠር የሚደረግ የውድድር አይነት ነው።