የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማሻሻል አዲስ የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጥ ተደረገ

65
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 በአገሪቱ እያጋጠመ ያለውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለማስተካከል አዲስ የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጥ ማድረጉን የኢትዮጵያ  ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ። የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ጣቢያዎችን በመክፈት በምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎች አደራጅቷል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቦርድ ሰብሳቢ የሳይንሰና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያና የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንዳሉት ተቋሙ በኔትወርክ ዝርጋታና በነበረው የአሰራርና የአደረጃጀት ችግር ምክንያት ለህብረተሰቡ የተፈለገውን ያህል አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቷል። ይህን ለማስተካከልም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች 11 ምክትል ስራ አስፈጻሚዎች መሾሙን ተናግረዋል። ከአሁን ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሲያጋጥም አዲስ አበባ ለሚገኘው ዋናው መስሪያ ቤት በማሳወቅ ችግሮችን ለመፍታት ይደረግ የነበረው አሰራር አድካሚና ረጅም ጊዜ ይወስድ እንደነበር አስታውሰዋል። አሰራሩ ያልተመቸና ዘመናዊነትን ያልተላበሰ በመሆኑ በተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ሲፈጥር መቆየቱን አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት በየክልሉ ምክትል ስራ አስፈጻሚዎች ራሳቸውን ችለው ግዥ፣ ግብዓት፣ የሰው ኃይል እንዲሁም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን መፍታት የሚያስችላቸውን አደረጃጀት በማዋቀር በቦርድና በመንግስት ጸድቆ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል። ይህም የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ያደርገዋል ነው ያሉት። እንደ ቦርድ ሰብሳቢው ገለጻ በየክልሉ ጣቢያዎችን በመጨመር ከክልል እስከ ወረዳ አደረጃጀት በመዘርጋት አገልግሎቱን ተደራሽ የማድረግ ስራ ይሰራል። የክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮዎች በዋናው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስር ቢሆኑም ለክልላቸው ነዋሪ የተሻለ አገልግሎትን ለመስጠት ታስቦ የተቋቋሙ ናቸው ብለዋል። ከዋናው መስሪያ ቤት ጀምሮ በክልልና በከተማ አስተዳደር በአግባቡ አገልግሎት በማይሰጡት ላይ የተጠያቂነት ስርዓት እንዲኖር እንደሚደረግም ኢንጂነር ጌታሁን ተናግረዋል። የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥና የተደራሽነት ችግር በስፋት ይስተዋላል። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ የአሰራርና የአደረጃጀት ማሻሻያዎች በማድረግ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተጨማሪ ጣቢያዎችን በመክፈት አገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ወደ ህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ዝግጁ ሆኗል። የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከዚህ በፊት የገንዘብ ችግር አንዱ ማነቆ እንደነበር የገለጹት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ አሁን ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍና ብድር በ375 ሚሊዮን ዶላር የማስፋፊያና ማሻሻያ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል። በዋናነትም በገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ አካባቢዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የፕሮጀክት ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከአውሮፓ ህብረት በዝቅተኛ ወለድ ብድር ለማግኘትና የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም