ቀጥታ፡

የአክሱም ቅርሶች ለከተማዋ ወጣቶች እንጀራ ናቸው

አክሱም የካቲት 28/2011የስልጣኔ ራስ እንደነበረች ዛሬም ቆመው ያሉ ሐውልቶቿ የሚመሰክሩላት ጥንታዊቷ የነገስታት መናገሻ አክሱም፤ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ እንግዶቿን 'አርሂቡ' ከማለት አትቦዝንም።

በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን 'ርዕሰ አድባራት ወገዳማት' አክሱም ጽዮን ማርያም ከአክሱም ሐውልቶች ፊት ለፊት ተጎራብታ በአንድ ስፍራ መገኘቷ ለጎብኝዎችም ሆነ ለአካባቢው ወጣቶች 'በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ' የሆነላቸው ይመስላል።

በከተማዋ ሰሜናዊ ምዕራብ ጎን ላይ በሚገኘው የሐውልቶችና የቤተ-ክርስቲያኗ መገኛ ስፍራ ላይ የእንግዶችና የአካባቢው ወጣቶች እንቅስቃሴን ማየት ሰርክ የተለመደ ነው።

በስፍራው የሚገኙ ወጣቶች ሕይወታቸው የአክሱማዊያን ፀጋ የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶችን ለማየት በሚመጡ እንግዶች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ከተማዋ ከምታገኘው ቁልፍ የቱሪዝም አገልግሎቶች ባሻገር ፎቶግራፍ ማንሳት፣ የጌጣጌጥ ቅርጻ-ቅርጽ ማውጣት፣ ባህላዊ አልባሳትና የከበሩ ድንጋዮች መሸጥ፣ የአስጎብኚነትና ሌሎች ከእንግዶች ጋር የተያያዙ ስራዎች ለወጣቶች እንጀራ ናቸው።

ከአካባቢው ከሚገኙ የድንጋይ አይነቶች በመፈልፈል መስቀል፣ የቁልፍ መያዣና ሌሎችንም ቅርጻ-ቅርጽ በመስራት የሚተዳደረው ወጣት ያሬድ ጥጋቡ በቀን ከ300 እስከ 400 ብር ገቢ እንዳለው ይገልጻል።

ወጣት መብራቱ ፍስሃ ደግሞ ከ2006 ዓ.ም በ15 ሺህ ብር በገዛው ግመል እንግዶችን በማዝናናትና የማስታወሻ ፎቶ እንዲነሱበት በማድረግ ከ30 እስከ 50 ብር እንደሚያስከፍል ገልጾ፣ ወደፊት ቤትና ተሽከርካሪ የመግዛት ዓላማ እንዳለው ይናገራል።

የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ክፍሌ ገብረሚካኤል ለ17 ዓመታት፣ በላይ ክንፈ ደግሞ ለ15 ዓመታት ጎብኝዎቹን ፎቶ በማንሳት ቤተሰብ እንደሚመሩ ይናገራሉ።

የሞባይል ስልክ ቴክኖሎጂ በፎቶ ስራ ላይ የራሱ አሉታዊ ጎን ቢኖረውም፤ ዛሬም ግን ሕይወታቸው እንግዶቹን ፎቶ አንስቶ በመስጠት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይገልጻሉ።

የፎቶ ስራ የራሱ ወቅታዊ ሁኔታዎች ቢኖሩም ገበያው መልካም መሆኑን ያነሳሉ።

ባለባጃጁ አትክልት አብርሃ አክሱም ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሰባት የጉብኝት ስፍራዎችና ወደ አየር ማረፊያ እንግዶችን ከወንድሙ ጋር በፈረቃ በማመላለስ ይሰራል።

የባጃጅ ስራ ወቅታዊና ገበያውም ተለዋዋጭ እንደሆነ የሚገልፀው አትክልት፤ በወቅቱ የአገሪቱ ሁኔታ የእንግዶች ፍሰት በአክሱም መቀዛቀዙን ይገልጻል።

ክፍሌ ገብረሚካኤልና አትክልት አካባቢው ሰላም በመሆኑ እንግዶች ጉብኝት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም