ቀጥታ፡

በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ተጥለው የተገኙት ሁለት ኢትዮጵያውያን ህጻናት አሳዳጊ አገኙ

አዲስ አበባ ካቲት 28/2011 ከሁለት ዓመታት በፊት በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ተጥለው የተገኙት ሁለት ኢትዮጵያውያን ህጻናት በስደተኞች መጠለያ ቆይተው አሳዳጊ በማግኘታቸው ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገቡ።

ህጻናቱ በቤት ሰራተኝነት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሄደው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተወለዱ መሆናቸው ታውቋል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በታህሳስ 2011 ዓ.ም በሪያድ የኢትዮ-ሳዑዲ የሠራተኛ የመነሻ ደመወዝ መጠን ዙሪያ ከመንግስት ጋር ለመደራደር ወደ ስፍራው አቅንተው ነበር።

በቆይታቸውም ህፃናቱ ተጥለው ከተገኙ በኋላ ሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የስደተኞች መጠለያ ይኖሩ እንደነበር ተመልክተዋል።

እድሜያቸው ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት የሚገመተው እነዚህ ሴትና ወንድ ህፃናት ከዓመታት የመጠለያ ካምፕ ቆይታ በኋላ በኢትዮጵያ አሳዳጊ በማግኘታቸው አዲስ አበባ ገብተዋል።

ህፃናቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ  ሲደርሱም የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

እንደ ዶክተር ኤርጎጌ ገለፃ ህጻናቱ ከአዋቂ ስደተኞችና የአዕምሮ ህሙማን ጋር ይኖሩ ስለነበር አሳዳጊ እንዲያገኙ የማፈላለግ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።

በዚሁ መሰረትም ሰላም የህጻናት መንደር ሁለቱንም ለማሳደግ ፈቃደኛ በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መደረጉን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ ሴቷን ህፃን ለማሳደግ የተረከቡ ሲሆን ሰላም የህጻናት መንደር ደግሞ ወንዱን ህፃን ለማሳደግ ተረክቧል።

ወደ ተለያዩ አገራት የሚሄዱ ዜጎች ህጋዊ መንገድን ተከትለው መጓዝ አለባቸው ያሉት ሚኒስትሯ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል

የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች አሳዳጊ ያጡ ህጻናት አሳዳጊ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩን ከምንጩ ለመፍታት ሚኒስቴሩ የሴቶችና ህጻናት መብት እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ነውም ብለዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ሱዳን ተጥለው የተገኙ ሁለት ኢትዮጵያዊ ህጻናትን በአገሪቷ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሽፈራው ጃርሶ ለማሳደግ ቃል መግባታቸውንና አስፈላጊው የህግ ሂደት ካለቀ በኋላ ልጆቹን እንደሚረከቡም ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ ህፃኗን በጥሩ እንክብካቤ ለማሳደግ ቃል በመግባት ተመሳሳይ የማሳደግ ሃላፊነት እየወሰዱ ያሉ ግለሰቦችም ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

የሰላም ህጻናት መንደር መስራች ወይዘሮ ፀሐይ ሮሽሊ ህጻናቱን የማሳደግ ጥያቄ ሲቀርብ ድርጅታቸው በደስታ እንደተቀበለው ገልጸው ተጥለው የተገኙ ህጻናትም እንዳሳዘኗቸው ገልጸዋል።

ህፃናቱ በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ተጥለው የተገኙት በ2009 ዓ.ም ሲሆን ሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የስደተኞች መጠለያ ታሳድጋቸው የነበረች እናት ሀፍሳ መሐመድ እና አሚር መሐመድ የሚል ስም አውጥታላቸዋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም