ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ስፖርትን ለማጠናከር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር መስራት መጀመሩን አስታወቀ

መቀሌ የካቲት 28/2011 በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የስፖርት ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር መስራት መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አስታወቁ፡፡

ኦሎምፒክ ኮሚቴው በትግራይ ለሚገኙ አራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያዘጋጀላቸውን የኦሎምፒክ ስፖርት  አምባሳደርነት ምስክር ወረቀት  ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እጅ ትናንት ተቀብለዋል፡፡

ዶክተር አሸብር በዚህ ወቅት  እንደገለጹት በሚቀጥሉት ዓመታት ጠንካራና ብዛት ያላቸው  ስፖርተኞች እንዲፈሩ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ስምምነት አድርገው እየሰሩ ናቸው፡፡

በትግራይና ደቡብ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስምምነት አድርገው ስራ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡

በሌሎች ክልል የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በተመሳሳይ ስራው እንደሚቀጥል ያመለከቱት ዶክተር አሸብር በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን  ለማፍራት አብረው እንደሚሰሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቃል እንደገቡላቸው አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከተመረጡት  ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መቀሌ፣ አክሱም፣አዲግራትና ራያ ዩኒቨርስቲዎች ይገኙበታል፡፡

ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለዩኒቨርስቲዎቹ ኃላፊዎች የምስክር ወረቀቱን  ከሰጡ በኋላ  የሀገር መልካም ስም የሚያስጠሩ ስፖርተኛች የሚፈሩ በትምህርት ቤቶች ነው" ብለዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዘርፉ ውጤታማነት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኦሎምፒክ ስፖርት አምባሳደር ምስክር ወረቀት  ከተሰጣቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  መካከል የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በሰጡት አስተያየት ሀገሪቱ  የምትፈልጋቸው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎችና አሰልጣኞች ለማፍራት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም